ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
በአንድ የሥራ አጋጣሚ ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ሲጓዙ በመንገድ ላይ ከተለያዩ እፅዋት ተቆርጠው እና ተቀርፈው የተዘጋጁ የጥርስ መፋቂያዎች ለገበያ ቀርበው ይመለከታሉ።
በወቅቱ እንደ ሌሎች መንገደኞች የመረጡትን መፋቂያ ሸምተው ጉዟቸውን ከመቀጠል ይልቅ የጥናት እና ምርምር ሰው እንደመሆናቸው ጥያቄ በውስጣቸው ተፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያ በርካታ ባህላዊ እውቀቶች እንዳሏት የሚያውቁት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ በውስጣቸው ለተፈጠረው “እነዚህ መፋቂያዎች ለጥርስ ንፅሕና እና ጤና መጠበቅ ምን ጥቅም ይኖራቸው ይሆን?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ምርምሬን ጀመርኩ ይላሉ።
ዘምባባ፣ ችፍርግ፣ ልምጭ፣ ወይራ፣ ዛህና እና ሌሎችም ከ20 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለጥርስ መፋቂያነት የሚጠቀሙባቸውን እፅዋት ዝርዝር በማዘጋጀት ጥናት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በጥናቱም እፅዋቱ በአፍ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችን በመግደል ለጥርስ እና ለድድ ጤና ከፍተኛ ጥቅም እንዳላቸው ማረጋገጥ ስለመቻላቸው ነው ተመራማሪው ለኢቢሲ ዶትስትሪም የገለፁት።
የጥናቱ ውጤትም ‘East African medical journal’ በተሰኘ መፅሔት ላይ መታተሙን ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገልፀዋል።
አክለውም በዘመናዊ መንገድ ተቀነባብረው ለጥርስ ንፅህና መጠበቂያ የቀረቡ ምርቶችን መግዛት የማይችሉ ሰዎች እፅዋቱን መጠቀም እንደሚችሉ በጥናት የተደገፈ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBCdotstream #Ethiopia #Ethnomedicine #Toothbrushsticks