የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ዋተር ጌት ሆቴል ተጀምሯል፡፡
በኮሚሽኑ የሚዲያ፣ ኮሙኒኬሽንና ተደራሽነት ዘርፍ አስተባባሪ ጌራ ጌታቸው ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለፁት፤ ከዳያስፖራው ጋር የተደረገው መድረክ ለሀገራዊ ምክክሩ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) አሜሪካ በዕድሜ ከኢትዮጵያ ያነሰች ብትሆንም በዴሞክራሲ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሷን አንስተው ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ስታሳልፍ በመቆየቷ በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
አሁን ግን “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲሉ የማንግባባቸውን እጅግ መሰረታዊ ምክንያቶች በሕዝባዊ ውይይት በመለየት ወደ ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር በጉዞ ላይ ነን ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህንን ጉዞ ለማሳካት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም ተቋቁሞ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን መስራቱን አንስተዋል፡፡
ይህ ሂደት ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ቅደመ ሁኔታና ልዩነት እየተሳተፉበት የሚገኙ ታሪካዊ ሂደት መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ምክንያቶች ቢሰደዱም የሀገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል በሚል በተለያዩ አማራጮች በምክክሩ ሂደት ለማሳተፍ ኮሚሽኑ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አንዳንዶች ይህንን የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ ለመግታት ቢንቀሳቀሱም ብዙዎች ግን ከኮሚሽ ጎን በመሆናቸው ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፤ ለዚህም አሁን ላይ በአሜሪካ እየተካሄደው ያለው መድረክ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በዴሞክራሲ ቁንጮ ላይ በምትገኝ ሀገር እየኖሩ መርህ አልባ የሆነ ተቃውሞ የሚጠበቅ አይደለም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ሂደቱን መደግፍ ባይቻል በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጓዝ ግን የተሻለው አካሄድ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይ በካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድንና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአካል ተገኝቶ ተመሳሳይ መድረክ እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ የቀሩት ሥራዎች ጥቂት ቢሆኑም እጅግ መሰረታዊ የሚባሉ ናቸው ያሉት ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር)፤ በቀጣይ የትግራይ ክልል ምክክር መድረክ ማከናወን፣ የዳያስፖራውን መድረክ ማጠናቀቅ እንዲሁም አጀንዳ መቅረፅና ዋናውን ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ አፈፃፀሙን መከታተል ዋና ዋና ተግባራቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡