በአማራ ክልል የተዘጋጀው አሻጋሪ የልማት ፍኖተ ካርታ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ የሚያስችል ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።
"አርቆ ማየት አልቆ መስራት" በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት ቀናት በክልሉን የ25 ዓመታት አሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ዙሪያ ለክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ ፍኖተ ካርታው ክልሉ ያለውን ፀጋና ተቋማዊ አቅምን በመጠቀም የማደግ ፍላጎትን ማሳካት ሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ፍኖተ ካርታው ክልሉን ከግጭት እና ከድህነት አዙሪት በማውጣት ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የዕቅዱ መዳረሻ ግብ በክልሉ ሁለንተናዊ የሆነ እድገት ማምጣት መሆኑንም ተናግረዋል።
ለውጤታማነቱ ዕቅዱን የሚፈፅም የአመራር ትጋትና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ዕቅዱ በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችሉ አሰራሮችን መያዙ ተመላክቷል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ