በሲዳማ ክልል በልማት መስኮች እየመጡ ያሉ ለውጦች የህዝቡን ታታሪነት እና የብልፅግና ፓርቲ የመደመር ፍልስፍና ውጤታማነት ማሳያ ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
በጉብኝቱ ወቅት አቶ አደም ፋራህ፤ በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማትና በተለያዩ የልማት መስኮች እየመጡ ያሉ ለውጦች የክልሉን ህዝብ ታታሪነት፣ የብልፅግና ፓርቲ የመደመር ፍልስፍና ውጤታማነት እንዲሁም ህዝቡ ለፓርቲው ራዕይ ስኬታማነት እየሰጠ ያለው ድጋፍ ድምር ውጤት ነው ብለዋል።
በሀዋሳ ከተማ እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን የፈጠረ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
አቶ አደም ፋራህ ከጎበኛቸው የልማት ስራዎች መካከል 70 በመቶ የተጠናቀቀው የ11 ነጥብ 2 ኪሎሜትር ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ይገኝበታል።
በብልፅግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፎ የተገነቡ የብልፅግና ቅርንጫ ፅህፈት ቤቶችንም አቶ አደም ፋራህ መርቀዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ የክልሉ ህዝብ በተለያዩ የልማት ሥራዎች እያደረገ ላለው ተሳትፎ አመስግነዋል።
በፈቃደአብ አለማየሁ