ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ሴክተር በተሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
32ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባዔው በዕውቀትና ክህሎት የበቃ ትውልድን በማፍራት ኢትዮጵያን ተምሳሌት ሀገር እናደርጋለን በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለትምህርት ሴክተሩ በተሰጠ ልዩ ትኩረት በከተማው በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል።
በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ሕብረተሰቡን በማስተባበር የትምህርት ቤቶች ደረጃ እንዲሻሻል መደረጉን አመላክተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለትምህርት አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች ምገባ፣ ዩኒፎርም እና የትምህርት ቁሳቁስ ግብዓቶችን በማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ መስራቱን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በከተማዋ በትምህርት ላይ በተተገበሩ ሥራዎች የ6ኛ እና 8ኛ ተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
ከ840 ሺ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ እና ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ተችሏል ብለዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በዐድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚካሄደው ጉባዔ የትምህርት ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን ማጠናከር እና የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።
በተጨማሪም በ2017 የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የትምህርት ባለድርሻዎች እውቅናና ሽልማት እንደሚበረከት ተገልጿል።
ሞላ ዓለማየሁ
#EBC #ebcdotstream #addisababa #education