ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ለዓመታት እየተፈራረቁ የነገሱበትን የስፔን ላሊጋ መልክ የቀየረ፣ አትሌቲኮ ማድሪድን ከተረሳበት ዳግም ወደ ዋንጫ የወሰደ ሰው ነው፡፡ አንድሪያ ቤርታ ይባላል፡፡ የተከታተለው ትምህረት ፈጽሞ ከስፖርት ወይም ከእግር ኳስ ጋር የሚገናኝ አደለም፡፡
በጣልያን ቤርሽያ የተወለደው ሰው ፊቱን ወደ እግር ኳሱ ከማዞሩ በፊት በሀገሩ የተለያዩ የገንዘብ ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ በዋናነት ግን ቴሪቶሪዮ ሎምባርዶ በተባለ ትልቅ ባንክ ውስጥ የቅርንጫፍ ሃላፊ ሆኖም አገልግሏል፡፡
የባንክ ባለሙያ እያለ በሰፈር የሚደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታችን ያስተባብር እና ያዘጋጅ የነበረው አንድሪያ ቤርታ ይሄ ጅምሩ ወደ እግር ኳስ አስተዳደር አድጎ በመጨረሻም ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ አስተዳደር ባለሙያ አንዲሆን አድርጎታል፡፡ በወቅቱ የሚሰራበትን የባንክ ሙያ ትቶ ወደ እግር ኳስ አስተዳደር ለመግባት መወሰኑን ለእናቱ ሲነግራት ፈጽሞ ያላመነችውና ያስደነገጣት ጉዳይ እንደነበር በአንድ ወቅት ተናግሯል፡፡
በክለብ ደረጃ የእግር ኳስ አመራርነት የጀመረው በጣልያ ካርፔንዶሎ ነው፡፡ በዚህ ክለብ ለአምስት አመት ሰርቷል፡፡ በወቅቱ የክለቡ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ሰው ኤነሪኮ ቪዮላ ካማርካ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አንድሪያ ቤርታ አንድ ተጫዋች ወደ ክለባችን ከመምጣቱ በፊት ስለ ብቃቱ ብቻ ሳይሆን ስለ ጸባዩ ጭምር ቤተሰቦቹን በአካል አግኝቶ እስከ መጠየቅ ይደርሳል ብለዋል፡፡ ዘመናዊ እግር ኳስ ለጥቃቅን ጉዳዮች ዋጋ የሚሰጥበት በመሆኑ በዚህ ዘመን ይሄ ቢደረግ አይገርምም የሚሉት ቪዮላ ከ20 ዓመት በፊት ግን ቤርታ ይሄንን ማድረጉ የወደፊቱን በሚገባ የተረዳ ሰው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ፓርማ ጄኖዋ እና አትሌቲኮ ማድሪድ የስፖርት ዳይሬክተር ሆኖ ያገለገለባቸው ክለቦች ናቸው፡፡
አትሌቲኮ ማድሪድ አንድሪያ ቤርታ ራሱን በሚገባ ለዓለም ያስተዋወቀበት ክለብ ነው፡፡ በ2013 የክለቡ የተጫዋቾች ምልመላ ዲፓርትንመንት ውስጥ በሀላፊነት ስራ ጀመረው ጣልያናዊ ከአምስት ዓመት በኋላ ግን የስፔኑ ክለብ የስፖርት ዳይሬክተር በመሆን ልዩነት ፈጣሪ ስራዎችን ከውኗል፡፡
ከአሰልጣኝ ዲያጎ ሲሚዮኒ ጋር በመሆን አትሌቲኮን ከመሀል ሰፋሪነት ወደ ዋንጫ የመለሰው ሰው በ12 ዓመታት የክለቡ ቆይታው ሁለት የላሊጋ፣ የስፔን ኮፓ ደልሬ እና ሱፐር ካፕ እንዲሁም የዩሮፓ ሊግ እና የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዋንጫውችን አሳክቷል፡፡ በተጨማሪም አትሌቲኮ ሁለት ጊዜ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ እንዲደርስ አድርጓል፡፡
አንድሪያ ቤርታ ባለው የመደራረድ እና የማሳመን አቅም በአነስተኛ ገንዘብ አስፈርሞ በውድ የሸጣቸው ከዋክብት በርካታ ናቸው፡፡ አንቱዋን ግሪዝማን፣ ሮድሪ እና ቶማስ ፓርቲ በቂ ማሳያ ናቸው፡፡ የ53 ዓመቱ ቤርታ በአትሌቲኮ ቤት ከ2015 እስከ 2024 ለተጫዋቾች ዝውውር ወጭ ያደረገው ገንዘብ ክሪስታል ፓላስ ካወጣው ያነሰ ነው፡፡ በ2019 በግሎብ ሶከር አዋርድ የአመቱ ምርጥ የስፖርት ዳይሬክተር ሆኖ ሽልማትም ተበርክቶለታል፡፡
የሚያስፈልገው ምርጥ ተጫዋች ሳይሆን ትክክለኛው ተጫዋች ነው የሚል መርህ ያለው ሰው ከእግር ኳስ ወኪሎች ጋር ባለው የጠበቀ ግንኙነት የሚፈልገውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ቃላ መጠይቆችን ማድረግ እና ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ብዙም መቅረብ የማይፈልገው ሰው ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ከተለያየ በኋላ በፒኤስጂ እና ማንችስተር ዩናይትድ ቢፈለግም አርሰናልን መርጧል፡፡
የአርሰናል የመጀመርያው የስፖርት ዳይሬክተር የነበረውን የቀድሞ ተጫዋቹን ኢዱ ጋስፐርን በመተካት ሰሜን ለንደን የደረሰው ጣልያናዊ የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ እስከ መዝጊያው ዕለት በአርሰናል ብዙም ባልተመለመደ መልኩ 8 ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡
እንደዚህኛው የክረምት የተጫዋቾች የዝውወር መስኮት ደጋዎቹን ጨምሮ በአርሰናል ዙሪያ ያሉ ሁሉ ደስተኛ የሆኑበት የዝውውር ጊዜ ያለ አይመስለም፡፡ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በተከፈተ ቁጥር ስራ የሚበዛበት ሰው እልህ አስጨራሽ የሆኑ ድርድሮችን ጭምር በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡
የጣልያን ሚዲያዎች በሚሰራው ጀብድ “ሚላግሮሶ ቤርታ” ወይም “ተአምረኛው ቤርታ” ብልው የሚጠሩት ሰው በዚህ ክረምት ከአርሰናል የለቀቁ ተጫዋቾችን በአንድ የዝውወር መስኮት ብቻ የተካበት እንዲሁም የቡድኑን ትልቁን የፊት መስመር ችግር የቀረፈበት መንገድ ገና ከአሁን የአርሰናል ደጋዎች ልብ ውስጥ እዲገባም አድርጎታል፡፡
በ17 ሚሊዮን ፓውንድ ከቫሌንሲያ የፈረመውን የ21 ዓመቱን ክርስቲያን ሞስኬራ ጨምሮ ሁሉም ወደ ሰሜን ለንደን የወሰዳቸው ተጫዋቾች በቋሚነት መሰለፍ የሚችሉ መሆናቸው ደግሞ አርሰናል ለዓመታት የነበረበትን የቡድን አማራጭ ችግር የሚፈታ ሆኗል፡፡ በቶማስ ፓርቴ ቦታ ማርቲን ዙቢሜንድኒ እና በሊጉ ትልቅ ልምድ ያለውን ክርስቲያን ኖርጋርድን ያስፈረመው ቤርታ ከአድካሚው የዮኬሬስ ዝውውር በፍጥነት እስከተፈጸሙት የኖኒ ማዱኬ እና ኤቤሬቺ ኤዜ ዝውውሮች ትልቁን የቤት ስራ በሚገባ ተወጥቷል፡፡
በአጠቃላይ ለ8 ተጫዋቾች ዝውውር 255 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭ ያደረገው አንድሪያ ቤርታ በተለይ በዝውውሩ የመዝጊያ ዕለት ፒዬሪ ሂንካፒዮን አስገዳጅ የመግዛት አማራጭ ባለው የውሰት ውል ማስፈረሙ ክለቡን ከየፋይናንስ ደንቡ ጋር እንዳይጋጭም አድርጎታል፡፡
ጨዋታዎች ባሉ ቁጥር ከስቴዲየሞች የማይጠፋው ዝምተኛው ተደራዳሪ የአርሰናልን የዋንጫ ጥማት ሊያስታግስ በመድፈኞቹ ቤት አጀማማሩን አሳምሯል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ