Search

ለሴት ሙስሊም ተጫዋቾች አርአያ የሆነችው ወጣቷ ኢቅራ ኢስማኤል

ሓሙስ ነሐሴ 29, 2017 244

ከእግር ኳስ ጋር የተዋወቀችው ገና በልጅነቷ ነው:: የቀድሞው የቼልሲ ኮከብ እና የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዲዲየር ድሮግባ አድናቂ ናት፡፡ በልጅነቷ እሱን እየተመለከተች አድጋለች፡፡ 

 

ኢቅራ ኢስማኤል ትባላለች፡፡ የተወለደችው በእንግሊዝ ለንደን ነው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነችው ኢቅራ ምንም እንኳን በእንግሊዝ ብትወለድም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወተችው ግን ለቤተሰቦቿ ሀገር ሶማሊያ ነው፡፡ 

 

በ2019 የሶማሊያ ብሔራዊ ቡድንን በአምበልነት እየመራች ጨዋታዎችን አድርጋለች፡፡

 

እግር ኳስን በ8 ዓመቷ የጀመረችው ኢቅራ እምነቷ በሚፈቅደው ሂጃብ አድርጋ እና ሰውነቷን ሸፍና ለበርካታ ዓመታት ተጫውታለች፡፡ 

 

የምዕራብ ለንደን ተወላጇ በአንድ ወቅት በእግር ኳስ ሜዳ የገጠማትን መሰናክል ያሸነፈችበት መንገድ ደግሞ ለብዙዎች ምሳሌ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

 

ሴት ሙስሊም ተጫዋቾች ብዙም ባልነበሩበት ጊዜ ኢቅራ ኢስማአል በተለመደው መልኩ ሂጃብ አድርጋ ሰውነቷን ሸፍና ወደ ሜዳ ለመግባት በመዘጋጀት ላይ እያለች የእለቱ ዋና ዳኛ እንደሌሎች ተጫዋቾች ቁምጣ ካለበስሽ ወደ ሜዳ መግባት አትችይም ይላታል፡፡ 

 

በለንደን የሴቶች ሊግ ተካፋይ ለነበረው ዩናይትድ ድራጎንስ የምትጫወተው ኢቅራ ለምን መጫዎት እንደማትችል ዳኛውን ትጠይቃለች ሱሪ ማድረግ የሚፈቀደው ለግብ ጠባቂዎች ብቻ በመሆኑ መሰለፍ እንደማትችል በድጋሜ ያስረዳታል፡፡ 

 

በተፈጠረው ነገር ግራ የተጋባችው ኢቅራ ኢስማኤል ጉዳዩን ለሀገሪቱ እግር ኳስ የበላ አካል ታመለክታለች፡፡

 

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበርም በፍጥነት የእስልምና እምነት ተከታይ እግር ኳስ ተጫዋቾችም ይሁኑ ወይም ሰውነታቸውን በጠባብ ሱሪ ሸፍነው መጫዎት የሚፈልጉ ተጫዋቾች መብታቸው መሆኑን ለሁሉም

የእግር ኳስ ማኅበራት መመሪያ አስተላለፈ፡፡

 

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር በተጨማሪም ቅሬታ ያቀረበችውን ኢቅራ ኢስማኤልን ይቅርታ በመጠየቅ እምነቷ በሚያዛት መልኩ ወደ ሜዳ መግባትና መጫዎት እንደምትችል አሳውቋታል፡፡

 

እግር ኳስ መጫዎት ለሁሉም የተፈቀደ ነው የምትለው 25 ዓመቷ ኢቅራ ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሳ ጨዋታዎችን አድርጋለች፡፡ 

 

ነገሮችን ከመፍራት የተነሳ ብቻ አለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴት እግርኳስ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ መሄድ እንደማይፈልጉ የምትገልጸው ወጣቷ ሁሉንም ነገር ተጋፍጠው ከፍላጎታቸው ጋር መገናኝት እንዳለባቸውም ትመክራለች፡፡

 

በምዕራብ ለንደን እንደመወለዷ የቼልሲ ደጋፊ የሆነችው ኢቅራ ኢስማኤል ሴት ሙስሊም እግር ኳስ ተጫዋቾች እምነታቸው የሚፈቅደውን አክብረው ወደ እግር ኳስ ሜዳ እንዲሄዱ ለብዙዎቹ አርአያም ሆናለች፡፡

 

የእግር ኳስ ሜዳ የሁሉም ሰው እንዲሆን እና እንደሷ ያሉ የእግር ኳስ ፍቅር ያላቸው ሴቶች በፈለጉት መንገድ እንዲጫዎቱ መንገዱን ማስተካከል ያስፈልጋል የምትለው ኢቅራ ኢስማኤል  አሁን  ላይ ፊቷን ወደ አሰልጣኝነት በማዞር የአሰልጣኝነት ኮርሶችን እየተከታተለች ትገኛለች፡፡

 

በአንተነህ ሲሳይ