ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም እና እድገት በጋራ እንዲቆም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።
1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጅድ እየተከበረ ይገኛል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ተወካይ ሼህ ፈቱዳን ሐጅ ዘይኑ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓሉ ነፃና ፍትሃዊ የመጅሊስ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ በተካሄበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
አክለውም ሌላው በዓሉን ልዩ የሚያደርገው በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት እውን የሆነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለሀገር አንድነት፣ እድገት እና ሰላም በጋራ መቆም ይገባልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የነቢዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ.) የልደት በዓል ስናከብር ለሰው ልጆች እኩልነት፣ ፍትህ እና ነፃነት የከፈለቱን መስዋዕትነት በመዘከርና በመተግበር እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡
በላሉ ኢታላ