Search

በሕዳሴው ግድብ ምረቃ ዋዜማ ላይ የሚከበረው የጉሙዝ ዘመን መለወጫ - "ጓንዷ"

ዓርብ ነሐሴ 30, 2017 33

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዋዜማ “ጓንዷ” የተሰኘው የጉሙዝ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ይከበራል።
የጉሙዝ ብሔረሰብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው።
ጓንዷ ከጳጉሜን 1 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ወራት በተለያዩ ትውፊታዊ ዝግጅቶች እንደሚከበር ታውቋል።
በጉሙዞች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው "ጓንዷ" የሰላም፣ የአንድነት እና የፍቅር መገለጫ በዓል ነው።
ጓንዷ ሰላም ፍቅር እና አንድነት ጎልተው ይንጸባረቁበታል ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች።
በበዓሉ የደረሱ የሰብል አይነቶች የሚቀመሱበት፣ የተለያዩ የብሔረሰቡ ባህላዊ ጭፈራዎች በአደባባይ የሚከወኑበት፣ ገንፎ፣ ቦርዴ፣ እንዲሁም የተለያዩ ከስጋ ምግቦች የሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች ተሰናድተው ጉሙዞች በፍቅር እና በአንድነት የሚያሳልፉበት ትውፊታዊ በዓል ነው- ጓንዷ።
በዓሉ ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ እስከ በተከታታይ ለሶስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ባህላዊ ክዋኔዎች እንደሚከበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ እና የበዓሉ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ መለሰ ኪዊ ገልጸዋል።
 
በጀማል አህመድ