Search

ፅናት የእነሱ መገለጫ የሆነው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

ቅዳሜ ጳጉሜን 01, 2017 70

ሀገራቸውን በወከሉባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ለሰንደቅ ዓላማቸው ሲሉ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል:: ወድቀዋል ተነስተዋል፡፡ ፅናትን በእጅጉ ከሚፈትነው አድካሚው ማራቶን እስከ ትራክ ውድድሮች መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ሁሉ ከፍለዋል፡፡

ለአፍሪካውያን አትሌቶች ፈር ቀዳጅ ከሆነው አትሌት አበበ ቢቂላ እስከ ማሞ ወልዴ፣ ከምሩፅ ይፍጠር እስከ ደራርቱ ቱሉ፣ ከኃይሌ ገ/ሥላሴ እስከ ፋጡማ ሮባ፣ ከገዛኸኝ አበራ እስከ ቀነኒሳ በቀለ እና ስለሺ ስህን እንዲሁም ከመሰረት ደፋር እስከ ጥሩነሽ ዲባባ እና ሌሎችም በርካታ አትሌቶች የሀገራቸውን ስም ከፍ ለማድረግ በፅናት የቆሙባቸው አጋጣሚዎች ባርካታ ናቸው፡፡ 

የሚገርመው ብዙዎቹ አድካሚ በሚባሉ ውድድሮች ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ብቻ ሳይሆን

ከህመም ጋር እየታገሉ ለሀገር የሚከፈለውን ዋጋ ለዓለም ያሳዩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ከኦሎምፒክ ጋር ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ከሚናፍቁት ነገር ግን ከማያሳኩት የወርቅ ሜዳልያ ጋር ያስተዋወቃት አትሌት አበበ ቢቂላ በፅናት የቆመባቸው እነዚያ የሮም ጎዳናዎች እንዴት ሊዘነጉ ደግሞስ ሊረሱ ይችላሉ፡፡ 

ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ባልተላቀቁበት በዚያ ዘመን አንድ ኢትዮጵያዊ ለዚያውም ለጥቂቶች ብቻ ትኩረት በሚሰጥበት የኦሎምፒክ መድረክ 42 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ማራቶን ያንን የሚያቃጥል አስፓልት በባዶ እግሩ ጨርሶ አሸናፊ መሆኑ ትርጉሙ ለአፍሪካውያን የአሸናፊነት ብቻ ሳይሆን የፅናት ምሳሌም ነው፡፡

ጊዜው ከ18 ዓመት በፊት ነው፡፡ በጃፓን ኦሳካ በተካሄደው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና በሴቶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ካጋጠማት የሆድ ህመም ጋር እየታገለች ያሸነፈችበት የሚረሳ አይደለም፡፡ 

ከፍተኛ የሆነ ሙቀት እና ወበቅ በነበረበት በዚያ ትልቅ መድረክ የሆድ ህመም ተጨምሮበት ውድድሩን ምን ያክል ፈታኝ እንዳደረገባት መገመት ከባድ አይሆንም፡፡

እጀግ ጠንካራ የሆኑ አትሌቶች በነበሩበት መድረክ ከህመም ጋር በመታገል አትሌቷ በፅናት የቆመችበት እና እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች በሀገር ፊት ሲሆኑ ምንም  መሆናቸውን አሳይታበታለች፡፡ 

ውድድሩን ካጠናቀቀች በኋላ በህይወቷ  እንዲህ አይነት ፈተና ገጥሟት እንደማያውቅ የገለጸችው ጥሩነሽ ዲባባ ፈተናውን በማለፍ በፅናት የቆመችው የሀገሯ ጉዳይ ስለሆነ እንጂ ሌላ መድረክ ቢሆን አቋርጥ ነበር በማለት መፅናት ለሀገር ያለውን ዋጋ በሚገባ ያሳየችበት ነው፡፡

የብዙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ታሪክ ይሄው ነው፡፡ 

በቡዳፔስት ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተመሳሳይ 10 ሺህ ሜትር የተሳተፈችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ 8 ዙር አካባቢ ሲቀር ጉልበቷ ላይ ጉዳት ያጋጥማታል፡፡  

አይደለም ከህመም ጋር እየታገሉ ይቅርና  በሙሉ  ጤና

እንኳን ሆኖ ፋታ የማትሰጠው አትሌት ሲፈን ሀሰን ባለችበት ውድድር ህመሟን ችላ የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደችበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በዚሁ መድረክ በሴቶች ማራቶን አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው አድካሚውን ውድድር ራሷን ስታ ጭምር የጨረስበት እና በፅናት የቆመችበትን ብዙዎች የሚዘነጉት አይደለም፡፡ 

አትሌት ቲኪ ገላና በለንደን ኦሎምፒክ ማራቶንን ስታሸነፍ በመውደቅ እና በመነሳት የታጀበ ነበር፡፡

የትራክ ንጉሡ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን ጨምሮ ብዙ አትሌቶች ትልልቅ መድረኮች በፅናት የመቆም ተምሳሌት ናቸው፡፡

በአንተነህ ሲሳይ