የጉሙዝ ብሄረሰብ አባላት አሮጌውን ዓመት ተሰናብተው አዲሱን የሚቀበሉበት በዓል ‘ጓንዷ’ ይባላል።
‘ጓንዷ’ ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ የጸደይ ወራት በተለያዩ ትውፊታዊ ዝግጅቶች ይከበራል።
የክረምቱና የጨለማው ወቅት ተጠናቆ በአዲሱ የብርሀንና የተስፋ ወቅት የሚብተው ‘ጓንዷ’ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ጎልተው የሚንጸባረቁበት ነው።
በዓሉ የደረሱ ሰብሎች የሚቀመሱበት፣ ገንፎ፣ ቦርዴ፣ እንዲሁም በተለያዩ የሥጋ ውጤቶች የሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች ተሰናድተው በፍቅርና በአንድነት የሚመገቡበት፣ የተለያዩ የብሄረሰቡ ባህላዊ ጭፈራዎች በአደባባይ የሚከወኑበት የጉሙዝ ብሄረሰብ ትውፊታዊ በዓል ነው።
የዘንድሮው የጓንዷ በዓል በዛሬው ዕለት የፌደሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ሀላፊ አቶ በላይ ወዲሻ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ቶማስ ቱት እና ሌሎች የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የብሄረሰቡ አባቶችና ጥሪ የተደረደረገላቸው አካላት በተገኙበት በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በክብረ-በዓሉ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ምስክያ አብደላ፣ የጉሙዝ ብሄረሰብ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታደሰ ዴሬሳ እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፥ ‘ጓንዷ’ የአንድነትና የዘመን መለወጫ በዓልን ባህላዊ ዕሴቶቹን በጠበቀ መልኩ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ አክለውም፥ በዓሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በዓሉን ማልማት፣ ማስቀጠልና መጠቀም ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በመርሐ-ግብሩ የብሄረሰቡ ትውፊታዊ የኪነጥበብ ሥራዎችና ባህላዊ ውዝዋዜዎች ለታዳሚያን ቀርበዋል።
በጀማል አህመድ
#EBCdotstream #BGRS #GumuzNewYear #Guandua