Search

ጉባዔዎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስምሪት ተደርጓል - የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ

እሑድ ጳጉሜን 02, 2017 77

ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ጉባዔዎች ያለምን የፀጥታ ችግር እንዲካሄዱ ለማድረግ ከጉባዔዎቹ ቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ እስከ ፍፃሜያቸው ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሰው ኃይል ስምሪት መደረጉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ጨምሮ የአፍሪካ-ካሪቢያን የመሪዎች ጉባዔ እና በቀጣይም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳሉ።
የፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ እና ደኅንነት ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ጉባዔዎቹ ያለምን የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲካሄዱ ለማድረግ ከጉባዔዎቹ ቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ እስከ ፍፃሜያቸው ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሰው ኃይል ስምሪት መደረጉን አመላክቷል።
በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ በርካታ የትራፊክ ፖሊሶች ስምሪት ወስደው የትራፊክ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጾ፤ መንገዶች እንዳይጨናነቁ ኅብረተሰቡም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቋል።
ኅብረተሰቡ እስከአሁን እያሳየ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረበው የፌዴራል ፖሊስ፤ በቀጣይ ለሚኖሩ አጠቃላይ የፀጥታ እና የትራፊክ ደንብ ማስከበር እንቅስቃሴዎች ኅብረተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።