የኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኅብረት ለኢትዮጵያ እድገት ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው በጣሊያን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ ገለጹ።
በጣሊያን ሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጳጉሜን 2 የኅብር ቀን በማስመልከት በጣሊያንና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተገኙበት በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡
በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም አንድ በሚያረጋቸው ኢትዮጵያዊነት ላይ በኅብረት በመቆም ለሀገራቸው እድገት ሊሰሩ እንደሚገባም አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ልማትና እድገት የሚረጋገጠው በሃገር ውስጥም በውጪም ያለው የኢትዮጵያ ጉዳይ ጉዳዬ ነው የሚል ሁሉ በኅብረት ሲቆም መሆኑን ነው የገለጹት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያንን ኅብረት እና ጥንካሬ እንደሚያመላክት የገለጹት አምባሳደሯ ኅብረ ቢሄራዊነታችንን የበለጠ በማጠናከር የበለፅገች ኢትዮጵያን መገንባት ይገባናል ብለዋል፡፡
በጣሊያንና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ እንደፈጸሙ ያስታወሱት አምባሳደር ደሚቱ ይህም ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጥሎ ከፍተኛው ተሳትፎ ነው ብለዋል።
ቤተልሄም ጥላሁን