Search

አፍሪካን እና ካሪቢያን ሀገራትን ጂኦግራፊ አለያይቶናል ታሪክ ግን አንድ አድርጎናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

እሑድ ጳጉሜን 02, 2017 93

አፍሪካን እና ካሪቢያን ሀገራትን ጂኦግራፊ ቢያለያያቸውም ታሪክ ግን አንድ አድርጎናል፤ በቀጣይም በተጠናከረ ትብብር መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ሁለተኛው የአፍሪካ ካሪቢያን ማኅበረሰብ የመሪዎች ጉባዔ "ለአፍሪካውያን እና ዘረ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትሕን ለመሻት አኅጉር ተሻጋሪ አጋርነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአፍሪካ እና የካሪቢያ ሀገራት ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉት በመለያየት ሳይሆን አንድ በመሆን ነው ብለዋል።
የመደመር እሳቤ የአላማ አንድነት መፍጠር መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እየተቀየረ በመሆኑ በአንድነት ድምፅ ማሰማት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ቀጣናዊ ትብብርን እንደሚፈልጉ አንስተው፤ አፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት ያላቸውን አቅም በማስተባበር አንድነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
ግብርና፣ ኢነርጂ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግር አፍሪካ እና የካሪቢያን ሃገራት የብልፅግና ድልድይ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ከትብብርም በላይ የጋራ ጥረት እና የአላማ አንድነትን በማጎልበት ሀሳብን በተግባር ወደ ዘላቂ ለውጥ እየቀየረች መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ስርዓተ ምህዳሩን መመለስ እና የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሏን አንስተዋል።
በአፍሪካ ትልቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በማስተሳሰር ቀዳሚ የትራንስፖርት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሕዝብ ለሕዝብ፣ እና የኢኮኖሚ ትብብር ፈጥሯል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ፋይናንስ ጉልበት እና መስዋዕትነት የተገነባ መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስንተባበር ጠንካራ እንደምንሆን አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ በስንዴ ምርታነት፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን በማስፋፋ፣ ሀገር በቀል መፍትሔዎች በመጠቀም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሰራቻቸውን ሥራዎችም አስረድተዋል።
እነዚህ ስኬቶች የመደመር ውጤቶች መሆናቸውን ገልፀው፣ በቀጣይ ከካሪቢያን ሀገራት ጋር ለጋራ ብልፅግና መተባበር አለብን ብለዋል።
አፍሪካ ከካረቢያን ሀገራት ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማጠናከር እንዳለባትም ገልጸዋል።
 
በሴራን ታደሰ