Search

ለኢትዮጵያውያንን ትንሣኤ ወሳኝ የሆነውን ኅብረት የምናስብበት የኅብር ቀን

እሑድ ጳጉሜን 02, 2017 289

ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ የእምነት፣ የብሔር እና የባህል ኅብር የሠራት የታሪክ ማማ የነፃነት ምድር ነች፡፡ ኢትዮጵያውያን ሲያብሩ ታሪክ እንደሚሠሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች አረጋግጠዋል፡፡

የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነው የዓድዋ ድል የተገኘው በኢትዮጵያውያን ኅብረት ነው፡፡ ኅብረት ያደምቃል፣ ኅብረት ያጠነክራል፣ ኅብረት ታሪክ ይሠራል፡፡ ለዚህም ነው ኅብረት ተአምር እንደሚሠራ የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን "ድር ቢያብር አንበሳን ያስር" የሚሉት፡፡

እነዚያ ቀጫጭን የሸረሪት ድሮች አንድ ላይ ሲጋመዱ ጠንካራውን አንበሳ የማሰር አቅም ያገኛሉ የሚለው ኅብርን በተገቢው መንገድ ይገልፀዋል። ኢትዮጵያውያንም እንደዚያው ናቸው፡፡

በተነጣጠሉባቸው ዘመናት በቀላሉ ለችግሮች እጃቸውን ሰጥተዋል፤ ባበሩባቸው ዘመናት ደግሞ ለሺህ ዘመናት ሊቆዩ የቻሉ ታአምራትን ሠርተዋል፡፡

 

የአክሱም ቅርሶች፣ የላሊበላ ውቅር፣ የጎንደር ስልጣኔ፣ የዓድዋ ዘመን ኢትዮጵያውያን በኅብር ሠርተው ለትውልድ ያስረከቧቸው ታሪኮች ናቸው፡፡

ዓድዋ ላይ በወቅቱ ኃያል የነበረችውን ጣሊያንን በማሸነፍ የነፃነት ፋናን የለኮሱት ኢትዮጵያውያን ሌላም ቀሪ ሥራ አለባቸው።

በጋራ ጠላትን በጦር ሜዳ ገጥመው ድል በመቀዳጀት ነፃነታቸውን ያወጁት ኢትዮጵያውያን ግን አብረው በመሥራት ሉዓላዊነታቸውን እና ነጻነታቸውን የተሟላ ለማድረግ ግን ሳይችሉ ለዘመናት ኖረዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ የረሃብ መገለጫ ሆና በመዝገበ ቃላት ላይ ምሳሌ እስከመሆን ደርሳም ነበር።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያውያን እየነቁ ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባ ወግ ቆይታቸው ላይ እንደጠቀሱት ኢትዮጵያውያን ባዳ እና ባንዳ ተባብረው ለዘመናት ያደረሱባቸውን ስብራቶች እየተረዱ መጥተዋል፡፡

"ኢትዮጵያውያን የባዳ እና የባንዳ ትስስር ህልሞቻቸውን ሲያጨናግፉባቸው የኖሩ ቢሆንም አሁን ግን የመንቃት እና የማደግ ዝንባሌ እያሳደጉ፣ ከዓለም ፍትሕን የመጠበቅ ዝንባሌን እየቀነሱ መጥተዋል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ኅብር ቀለም ብቻ ሳይሆን ክንድም ነው፤ በጋራ ድኅነት የሚደቆስበት ክንድ፣ በጋራ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ የሚሠራበት ኃያል ክንድ፣ ሀገርን አንገት ከመድፋት የሚታደጉበት ክንድ ነው!

ብዙ መልክ አንድ ሕዝብ የሆኑት ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተባብረው ክብራቸውን የሚመልሱበት፣ የሀገራቸውን ትንሣኤ የሚያረጋግጡበት ዘመን ላይም ይገኛሉ፡፡

አብረው የነበሩት፣ አሁንም አብረው ያሉት የኢትዮጵያ ልጆች የትላንቱን ታሪካቸውን ለነገ መመሪያ በማድረግ ኅብራቸውን የታላቅነት መገለጫ የትውልድ መኩሪያ ሊያደርጉት ተነስተዋል፡፡

 

አሮጌው ዓመት አብቅቶ አዲሱ ዓመት ሲመጣ በተስፋ መሻገር ልማዳቸው የሆኑት ኢትዮጵያውያን ታሪክ በገመደው ኅብረታቸው ከድህነት ወደ ብልጽግና ለመሻገር እንደሚችሉ አምነው ታጥቀው መነሳት እንዳለባቸው ይታመናል፤ ምክንያቱም ይህ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

አያቶች ኅብረታቸውን አጠናክረው ዓድዋ ላይ ጠላትን እንዳንበረከኩ ሁሉ ዛሬም የልጅ ልጆቻቸው በፊናቸው ደግሞ ዓባይን ጉባ ላይ አሳድረውታል። ይህን ዕውን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በኅብር ክንዳቸው ድኅነት ታሪክ በማድረግ የሀገራቸውን  ትንሣኤ ማብሰር አይሳናቸውም፡፡

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #unity #unityindiversity #ጳጉሜን #የኅብር_ቀን