ህንግጫ በመባል የሚታወቀው የኮንታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም ልጆች በተገኙበት ኮንታ ዞን ዋና ከተማ በአመያ እየተከበረ ይገኛል።
የኮንታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በተለይ ወጣቱ ባህላዊ እሴቶቹን ጠብቆ ቀጣዩን ዓመት የሚቀበልበት የሰላም፣ የእርቅ እና የአንድነት በዓል ነው።
በበዓሉ የብሔሩን ባህል፣ ታሪክ እና ወግ የሚገልጹ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦችና ሌሎች ቁሳቁስ ቀርበው በታዳሚዎች እየተጎበኙ ነው።
የህንግጫ በዓል የብሔሩ ተወላጆች ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁባቸው የተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚካሔዱበት ጭምር ነው።
በዓሉ ባህላዊ ዳራው ተጠብቆ እና ህዝባዊ መሠረቱን ይዞ እንዲቀጥል እየተሠራ ስለመሆኑ ተገልጿል።
የህንግጫ በዓል ዋና ዓላማ ሰዎች ከጥላቻ እና ከክፋት በመውጣት በእርቅ፣ በፍቅር እና በሰላም አዲሱን ዓመት እንዲቀበሉ ማድረግ መሆኑን በበዓሉ ላይ የተገኙት ቄስ ጎዶቶ ተናግረዋል።
በዓሉ ሰዎች በአዲስ መንፈስ እና በአዲስ ስሜት ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገሩበት የአንድነት በዓል መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል።
በዓሉ ከምስጋና፣ ከሰላም እና ከእርቅ ባሻገር የተለያዩ ጨዋታዎችን በማካተት እስከ መስቀል ይዘልቃል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ