ዛሬ (መስከረም 2 ቀን 2018 ዓ.ም) 90ኛ ዓመቱን የያዘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ከብዙዎች አዕምሮ ውስጥ የማይጠፉ ፕሮግራሞችን ይዞ ለዓመታት ዘልቋል።
‘ከመጻሕፍት ዓለም’ ደግሞ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ከቀሩ ወርቃማ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራሞች አንዱ ነው።
"ከመጻሕፍት ዓለም! - በዚህ ከመጻሕፍት ዓለም በተሰኘ ፕሮግራም በልዩ ልዩ ደራሲያን የተጻፉ ልብ ወለድ ድርሰቶች እና ሌሎች ሥነ-ጽሑፎችም ይቀርባሉ” በሚል በደጀኔ ጥላሁን ማራኪ ድምፅ ሲተዋወቅ የነበረው ይህ ፕሮግራም ዛሬ ላይ በበርካቶች ጆሮ ውስጥ ማቃጨሉ አይቀርም።
ውብ የሆኑ የእሑድ ምሽቶች እና የሰኞ ማለዳዎች ትውስታ የሆነው የከመጻሕፍት ዓለም ፕሮግራም፣ ብዙ ልብ አንጠልጣይ ልብ ወለዶችን፣ ወጎችን፣ ግጥሞችን እና ሌሎች መጣጥፎችን ከሕዝብ ጋር አስተዋውቋል።
ፕሮግራሙ፣ ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት እና የተለያዩ የሀገራችን አርቲስቶችን ብሎም ጋዜጠኞችን በትረካ ያገናኘ ድንቅ ዝግጅት ነበር።
ፍቅር እስከ መቃብር፣ የታንጉት ምሥጢር፣ የተሸጠው ሰይጣን፣ ከአድማስ ባሻገር፣ ምንዱባን፣ ሳቤላ፣ ብርቅርቅታ፣ የኅሊና ደወል፣ ሳይላክ የቀረ ደብዳቤ፣ በኑሮ ሸለቆ ውስጥ፣ የሕይወት ጠብታዎች፣ መርበብት፣ ዝጎራ፣ ኦሮማይ፣ ጥቁር ደም፣ ሰመመን፣ ቆንጆዎቹ፣ የቬኑሱ ነጋዴ፣ ማሕሌት፣ ቃልኪዳን፣ መከረኞች፣ ወንጀለኛው ዳኛ፣ ሾተላዩ ሰላይ፣ የውበት ወጥመድ እና ሌሎች ልበወለድ ድርሰቶችን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይተረኩ ከነበሩት ውስጥ ናቸው።
ደጀኔ ጥላሁን፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ፈቃዱ ተክለማርያም፣ ዓለምፀሐይ በቀለ፣ ሐረገወይን አሰፋ እና ሌሎችም በማራኪ የአተራረክ ሥልታቸው የምናስታውሳቸው፤ የሚናፈቁ ድምፆች ነበሩ።
በተለይም ሐረገወይን አሰፋን እና ደጀኔ ጥላሁንን በምንዱባን ትረካ ብዙዎች ያስታውሷቸዋል፤ በትዝታ ፈረስ ወደኋላ ተመልሰው “የምንዱባኑ ዣን ቫልዣ ራሱ ደጀኔ ጥላሁን ነበር የሚመስለን” ሲሉ አሁን ድረስ የሚያስታውሱ አሉ።
የኢትዮጵያ ሬዲዮ በዚሁ ከመጻሕፍት ዓለም አማካኝነት በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ‘የክፍለ ዘመኑ ጀግና’ የሚል እውቅና አግኝቷል።
ብዙዎች “በአንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ከመጻሕፍት ዓለም ፕሮግራም ልጅነታችንን ያስታውሰናል” ይላሉ።
እርስዎስ ከመጻሕፍት ዓለም ሲነሣ ምን ያስታውሳሉ? ትዝታዎን ያጋሩን!
በሔለን ተስፋዬ