በሐረር ከተማ የወንዝ ዳርቻ ልማትን በስፋት ተግባራዊ በማድረግ ለዘላቂ የአካባቢ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በሐረር ከተማ የወንዝ ዳርቻ ልማት ማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በ6 ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን መሆኑ በከተማ ማዘጋጃ ቤቱ በቀረበው ዲዛይን ተመላክቷል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በዚህ በወቅት እንደተናገሩት የወንዝ ዳርቻ ልማት ለነዋሪው ጤናማ ሕይወት እና ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ወሳኝ አስተዋፅኦ ከማበርከቱም በላይ የከተማዋን ገፅታ የመቀየር አቅም አለው።
በተለይ ከተማዋ ንፁህ ወንዞች የሚፈሱባት፣ ፅዱና ውብ እንድትሆን በማስቻል ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
ይህን እውን ለማድረግም ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾችን በአግባቡ ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በቀጣይ በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ እንዲገባም ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በቴዎድሮስ ታደሰ