ይህ ዓይነ ገብ የሆነ የሆነ ለምለም አረንጓዴ ስፍራ የሚገኘው በአፋር ክልል፣ ሀሪ-ረሱ ዞን፣ ሰሙ-ሮቢ ገለኣሉ ወረዳ ነው።
ወረዳዋ ሰሙ-ሮቢ የሚለውን ስያሜዋን ያገኘችው በአካባቢው ከሚገኘው ‘ሰሙ’ ተራራ እና ወረዳዋን አቋርጦ ከሚያልፈው ‘ሮቢ’ ወንዝ እንደሆነ በአካባቢው ማህበረሰብ ይነገራል።
ከሰሙ ተራራ ስር የምትገኘው ወረዳዋ ከሮቢ ወንዝ ውሃ እየጨለፈች ሁለ-ገብ የግብርና ሥራን በስፋት በማከናወን ላይ ትገኛለች።
በወረዳዋ በመስኖ እና በክረምት ዝናብ ከ5 ሺህ 200 በላይ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ እንደሚገኝ የወረዳዋ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ መሐመድ ዬሴጌሌ ለኢቲቪ ተናግረዋል።
አካባቢው ለግብርና ምቹ በመሆኑ ኅብረተሰቡን ከተረጅነት ለማውጣት መንግሥት በወረዳዋ ከትናንሽ ማሳዎች እስከ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በወረዳዋ ማሾ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ እና የተለያዩ ቋሚ ተክሎች እየለሙ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።
በአፋር ክልል በ2018 የምርት ዘመን በአጠቃላይ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
በክልሉ ከፍተኛ የክረምት ዝናብ በሚያገኙት ኪልበቲ-ረሱ እና ፈንቲ-ረሱ ዞኖች ላይ የተለያዩ ሰብሎች እየለሙ ይገኛሉ።
በክልሉ በመኸር ወቅት በዘር ለመሸፈን ከታቀደው መካከል ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን መቻሉ ተገልጿል።
በመካከለኛው እና በታችኛው አዋሽ አካባቢዎች ከከፊል አርሶ አደሮች እስከ ኢንቬስተሮች በመስኖ ልማት የተለያዩ ሰብሎችን እና ለምግብነት የሚውሉ ቋሚ ተክሎችን በማልማት ላይ ናቸው።
በአጠቃላይ በክልሉ የኅብረተሰቡን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ከተረጂነት ለመላቀቅ እየከናወነ ባለው ሥራ አበረታች ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑንም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።
በሁሴን መሐመድ
#EBCdotstream #Afar #Agriculture