Search

ኢሬቻ ሁሉም በነጻነትና በእኩልነት የሚያከብረው በዓል ነው

ማክሰኞ መስከረም 20, 2018 3788

ኢሬቻ ሕብረ ብሔራዊነት የሚንጸባረቅበት፣ ሁሉም በነጻነትና በእኩልነት የሚያከበረው በዓል መሆኑን የቢሾፍቱ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገነት መኮንን ገልጸዋል፡፡
ኢሬቻ የወንድማማችነት፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የነጻነት እና የእኩልነት ምልክት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት በብሔር ብሔረሰቦች በባህላዊ አልባሳት ደምቀው የሚታዩበት በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በመፍጠር፣ አብሮነትንና አንድነትን የሚያጎላ እንዲሁም መተሳሰብን የሚጨምር ነው ብለዋል፡፡
አባገዳዎች የሁሉም አባት፤ ሃደ ስንቄዎች የሁሉም እናት ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ በባህሉ ሁሉም በልቶ፣ ሁሉም እኩል ልጅ ሆኖ የሚያድግበት እሴት መኖሩን በመግለጽ፣ ይህም በበዓሉ እንደሚንጸባረቅ ነው በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም የገለጹት፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ ለሚከበረው የሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል፣ እንግዶችን ለመቀበል በተቀናጀ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የቢሸፍቱ ከተማ በኮሪደር ልማት እምርታን እያሳየች ባለችበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ኃላፊዋ፤ ኢሬቻ የሚከበርበት ሆራ አርሰዴ ሐይቅ ለበዓሉ ታዳሚዎች ምቹ ተደርጎ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችሉ ሆቴሎችን፣ የእንግዳ ማረፊያዎችን፣ የምግብ እና የመጠጥ አቅርቦትን እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን በማሟላት ቅድመዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የዘንድሮው የሆራ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል የፊታችን እሁድ መስከረም 25 ቀን በቢሸፍቱ ሆራ አርሰዴ ይከበራል፡፡
መሀመድ ፊጣሞ