Search

ትውልዱ ኢሬቻን የመሰሉ በጎ ማህበራዊ እሴቶችን መጠበቅ እና ማሳደግ አለበት

ማክሰኞ መስከረም 20, 2018 58

የኢሬቻ በዓል ማህበራዊ ትስስርን የማጠናከሪያ አንዱ መድረክ እየሆነ በመምጣቱ፣ የአሁኑ ትውልድ ኢሬቻን የመሰሉ በጎ ማህበራዊ እሴቶችን መጠበቅ እና ማሳደግ አለበት ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ።
የጉሚ በለል ውይይት "ኢሬቻ ለሀገር እድገት እና አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እና ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ ኢሬቻ በርካታ በጎ እሴቶች ያሉት መሆኑን በመግለጽ፣ ኢሬቻን የመሰሉ በጎ ማህበራዊ እሴቶችን መጠበቅ እና ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የዘርፉ ምሁራንም የኢሬቻን ምንነትና ትክክለኛ መገለጫዎችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ማሳወቅ እና ማስገንዘብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ውይይቱ በኢሬቻ ቱሩፋቶች እና ምንነት ላይ ያተኮረ ሲሆን ኢሬቻ የኢትዮጵያን የአንድነት እና የአብሮነት ባህል ለዓለም የሚያሳይ መሆኑ ተነስቷል።
ኢሬቻ የአብሮነት፣ የአንድነት እና ሁሉም የሚሳተፉበት በዓል በመሆኑ፣ የሃገርን አንድነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ትምህርት መምህር በሆኑት መሐመድ ነሞ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምብሩ፣ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች እና ምሁራን ተገኝተዋል።
በአሊ ደደፎ