የዓለም የአረጋዊያን ቀንን በማስመልከት በአፋር ክልል አዋሽ አርባ ከተማ ለአረጋዊያን የማዕድ ማጋራት፣ የገንዘብ፣ የአልባሳት እና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የዓለም የአረጋዊያን ቀን በክልል ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ "ለአረጋውያን ደህንነት መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዋሽ አርባ ከተማ አቡነ ዮናስ የአረጋዊያን እና ህፃናት መርጃ ማዕከል ተከብሯል።
ቀኑን ምክንያት በማድረግ በክልሉ በ6 ወረዳዎች ለሚገኙ 100 ለሚሆኑ አረጋዊያን በአጠቃላይ የ200 ሺህ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
አረጋዊያኑን በተለየ መልኩ ለመደገፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ማህበራዊ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ነስሮ ኡዳ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የአረጋዊያን መረጃ ማዕከላትን ለመደገፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአዋሽ አርባ እና አዋሽ ሱባህ ኪሎ ከተማ ለሚገኙት የአረጋዊያን መርጃ ማዕከላት ለእያንዳንዳቸው የመቶ ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።
በመከላከያ ሠራዊት የአዋሽ አርባ ውጊያ እና ቴክንክ ትምህርት ቤት ኃላፊ ብ/ጄኔራል ታዬ አለማየሁ በበኩላቸው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በየአካባቢው በጎ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ሠራዊቱ በተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎች ማለትም በመጠጥ ውኃ፣ ጤና፣ መንገድ፣ ትምህርት ልማት እንዲሁም አረጋዊያን በመደገፍ እና በሌሎች ሥራዎች በስፋት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአዋሽ አርባ ውጊያ እና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ለእነዚህ አረጋዊያን በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ይህን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የአረጋዊያን ማዕከላትን በግል፣ በድርጅት እና በማህበር እየደገፉ ለሚገኙ አካላት የምስጋና እና እውቅና ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሁሴን መሐመድ