Search

ኢሬቻ ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል፦ የቱሪዝም ሚኒስቴር

ማክሰኞ መስከረም 20, 2018 64

ኢሬቻ በሃይማኖት እና በብሔር ልዩነት ሳይገድብ የሚከበር እና ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ሚና የሚጫወት በዓል ነው ሲል የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተሾመ ተክሉ ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ኢሬቻ ሕዝባዊ ሁነት እንደመሆኑ የቱሪስቶችን ቀልብ እንደሚስብ ተናግረዋል።

ኢሬቻ የራሱ የሆነ ቀለም እና ይዘት እንዲሁም ትውፊታዊ ክንውኖች ያሉት ሕዝባዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሁነት ስለመሆኑም ነው የገለጹት።

ኢሬቻ ፈጣሪ የሚመሰገንበት የአደባባይ በዓል ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ የበዓሉ አክባሪዎች አለባበስ እና ክወና ሳቢ መሆኑን አክለዋል።

ይህም የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር ለዘርፉ እና ለሀገሪቱ ትልቅ የሀብት ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ነው አቶ ተሾመ የተናገሩት።

ኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔ የፊታችን ቅዳሜ፤ ኢሬቻ ሆረ ሀርሰዲ ደግሞ በማግስቱ እሑድ ዕለት እንደሚከበሩ ይታወቃል።

በሜሮን ንብረት

#EBCdotstream #Irreecha #celebration #tourism