Search

ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት የጥበብ ስፍራዎች

ረቡዕ መስከረም 21, 2018 44

በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ያሉ የጥበብ ስፍራዎች ተተኪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የኪነ ጥበብ እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገለጹ።
አርቲስት ሺመላሽ ለጋስ፤ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ኮምፕሌክስ ተመርቆ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
እንደዚህ ዓይነት የኪነ ጥበብ ማሳያ መሰረተ ልማቶች ትውልዱን በስነ ምግባር እና በኪነ ጥበብ ለማነጽ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የቴአትር ኮምፕሌክሱ የከተማዋን ህጻናት እና ወጣቶች ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ ከሰባት ዓመት በፊት ከኪነ ጥበብ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የነበረው ተግዳሮት የጥበብ ስራዎች የሚቀርቡባቸው ቦታዎች እጥረት መሆኑን ገልጸዋል።
በመዲናዋ የነበሩ የኪነ ጥበብ ማሳያ ቦታዎች ሁለገብ ያልሆኑ እና በቴክኖሎጂ ያልተደገፉ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በፍጥነት እና በጥራት እየተገነቡ ያሉ የኪነ ጥበብ ማሳያ ቦታዎች ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የህጻናት እና ወጣቶች ቴአትርም ፕሮፌሽናል የሆኑ ባለሙያዎችን ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመላክተዋል።
በቀጣይ የሚጠብቀን ፈተና በስራዎቻችን ጥራት እንጂ በኪነ ጥበብ ስፍራዎች እጥረት አይደለም ያሉት ጋዜጠኛ ጥበቡ፤ መሰል ማዕከላትን በተለያዩ አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ተዋናይ ትዕግስት ሌሊሳ በበኩሏ፤ የኪነ ጥበብ ማሳያ መሰረተ ልማቶች ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ብላለች፡፡
በተለይም የህፃናት እና የወጣቶችን የኪነ ጥበብ ብቃት በማጎልበት ረገድ ትልቅ አቅም መፈጠሩን ጠቅሳለች።
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁማ፤ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የሚመጣው ተተኪ ትውልድ በዚህ ረገድ እድለኛ መሆኑን ተናግራለች።
ከዚህ ቀደም በከተማዋ ግዙፍ የኪነ ጥበብ ማሳያ ስፍራዎች እንዳልነበሩ የገለጹት ደግሞ የቴአትር እና የሙዚቃ ባለሙያው አርቲስት ጸጋዬ ዘርፉ ናቸው።
መንግስት ለኪነ ጥበብ ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ለባለሙያውም ሆነ ለተመልካቹ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡
ይህም በቀጣይ ወጣቶች ዘርፈ ብዙ የኪነ ጥበብ ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ እንደሚያስችል ተናግረዋል።