Search

የቤቶችን ግንባታ በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን የሚረዱ ዘመናዊ ማሽነሪዎች ወደ ሥራ ገቡ

ረቡዕ መስከረም 21, 2018 41

የቤቶችን ግንባታ በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን የሚረዱ ዘመናዊ ማሽነሪዎች እና ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት በተሰጠው የቤቶች ልማት፣ የቤት ፍላጎት አቅርቦት ክፍተትን ለመሙላት ሁሉንም ማሕበረሰብ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አማኑኤል አያሌው በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም የቤቶች ግንባታ ሥራዎችን ለውጭ አካላት በኮንትራት ይሰጥ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ ግን የግንባታ ሂደቱን ሊያሳልጡ የሚችሉ ዘመናዊ የግንባታ መሳሪያዎችን በእጁ በማስገባቱ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ኮርፖሬሽኑ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ጠቅሰው፣ ከራሱ ባለፈ ለሌሎችም እንደሚያቀርብ ነው አቶ አማኑኤል የገለጹት፡፡
የግንባታ ማሽነሪዎቹ በራሱ የገቢ አቅም የተገዙ መሆናቸውን በመግለጽ በቀጣይም በርካት ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስገባ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሀገር በተለይም በአዲስ አበባ የቤቶች ልማት አንገብጋቢ መሆኑን በመለየት፣ በመንግስት የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት በኮርፖሬሽኑ በኩል ወደ ተግባራዊ ሥራ እንዲሸጋገር እየተሰራ መሆኑን አቶ አማኑኤል ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዜጎችን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል፣ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የቤቶች ልማት እንደሚከናወን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ