Search

ለውጥን የሚሻው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

ሓሙስ መስከረም 22, 2018 254

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የጠና ህመም ላይ ለመሆኑ የተለየ የህክምና ማረጋገጫ አያስፈልግም፡፡ አሁንም ባለፉት ዓመታትም በትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች የተመዘገቡትም ይሁኑ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

በቅርቡ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከ34 ዓመት በኋላ ወርቅ ሳታገኝ የተመለሰችበት ሆኗል፡፡ በረጅም ርቀቶች በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ተአምር የሰሩ ጀግኖችን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ አሁን በእርግጠኝነት የእኔ የምትለው ዲስፕሊንም ይሁን የምትተማመንበት አትሌት አለ ወይ የሚለው ጉዳየይ ትልቅ መልስ የሚፈልግ ነው፡፡ 

 

ለመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የገጠመው ፈተና ምንድን ነው ?

 

ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞች፣ አትሌቶች፣ አመራሮች፣ ራሱ ፌደሬሽኑ እንደ ተቋም እና በዙሪያው ያሉ ሰዎች አትሌቲክስን የሚረዱበት መንገድ ብዙ ጥናት የሚፈልግ እና አስችኳይ መፍትሄ የሚሻም ይሆናል፡፡ 

 

ኢትዮጵያ ከዓለም 22ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበትን የቅርቡን የዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና እና ፌደሬሽኑ የሰጠውን መግለጫ ለመነሻነት ያክል እንመልከት፡፡

 

የስልጠና መንገድ፣ የአትሌቶች እና አሰልጣኞች ለፌደሬሽኑ ደንብ ተገዥ አለመሆን፣ ሀገራዊ ስሜት መቀዝቀዝ፣ ግለኝነት፣ የጥቅም ግጭት፣ የብሔራዊ አትሌቶች መበተን፣ የእውቀት ማነስ፣ ተጠያቂነት ዕጦት እና ሌሎች ጉዳዮችም የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ኮማንደር ስለሺ ስህን አሁናዊ ዋና ችግሮች መሆናቸውን ተናግሯል።

 

ስልጠናን ብቻ ነጥለን ካየነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሚታየው እና ከሚጨበጠው ነገር የወጣ አይደለም፡፡ ማለትም የተመቻቸ የማዘውተሪያ ቦታ ብቻ እንጂ ከዚያ ውጭ ያሉትን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት መሆኑን እና ወደ ሚፈለገው ውጤት የሚወስድ መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ዓለም ለጥቃቅን ጉዳዮች (quite details) ትርጉም ሰጥቶ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እኩል በመራመድ ለአሸናፊነት በሚዘጋጅበት ይሄኛው ዘመን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ግን ባለበት ቆሟል፡፡ 

 

በተለይ ደግሞ Artificial intelligence (AI) በመታገዝ የሚሰጡ ስልጠናዎች የዓለምን የስፖርት ታሪክ ሌላ መልክ ማስያዛቸው አሁናዊውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከቀደሙት ለማድረስ ከተንቀረፈፈበት ሩጫ በብዙ መፍጠን እንደሚገባው ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

 

አሁንም እንደ ቀደመው ዘመን ሁሉ ቤትን ዘግቶ (ከዓለም ተነጥሎ) ትራክ እና ጎዳና ላይ ሰዓት  በመያዝ ብቻ የሚሰጥ ስልጠና ብዙ ርቀት የሚያስጉዝ ባለመሆኑ አሰልጣኞች እና አትሌቶች ራሳቸውን ለአዳዲስ ነገሮች በማዘጋጀት ቀድመው መገኘት ግድ ይላቸዋል፡፡

 

የረጅም ርቀት አትሌቶችን ከመካከለኛ ርቀት  ወይም ከሌላ የውድድር ዓይነት ጋር በጋራ ማሰራት አንዱ ርቀት የሚፈልገውን የተለየ ባሕርይ እና ጥቃቅን ጉዳይ በውል አለመረዳትም ይሁን አውቆ ነገሩን ችላ ማለት በስፋት የሚስተዋሉ ጉዳዮች ናቸው።

 

ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመጡ ቁጥር በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ችግሮች እና  መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች፡፡ 

 

አንደኛው እና ዋነኛው ጉዳይ የአትሌቶችም ይሁን የአሰልጣኞች የመምረጫ መስፈርት ግልጽነት የጎደለው ከመሆኑ ባሻገር ለቅሬታ በር የሚከፍት መሆኑ ውጤቱ ላይ ብቻ ሳይሆን የስልጠና መንገዱ ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ አሁን እየተሰራበት ያለው መስፈርት ብዙ ማሻሻያዎችን የሚፈልግ ሲሆን በተለይ የአሰልጣኞች ደረጃ፣ ያላቸው የትምህርት ዝግጅት እና ውጤታማነት እንዲሁም የአትሌቶችን ወቅታዊ ብቃትን በሚገባ የሚያሳይ እና  የሚመዝን መሆን ይጠበቅበታል፡፡

 

ሌላኛው ራሳቸውን ከፌደሬሽኑ በላይ አድርገው ያስቀመጡ ወይም ጠቅላላ ጉባኤው እና  ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ላወጣው ደንብ እና መመሪያ ተገዢ የማይሆኑ ባለሙያዎች  ጉዳይም በዚያው ልክ መፍትሄ ማግኘት ያለበት ነው፡፡ 

 

ለማሳያ ያክል በቅርቡ በተደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  የተመረጡ አሰልጣኞች እቅድ እንኳን ለማቀድ በፍጹም ፍላጎት የሌላቸው እንደነበሩ የፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት መናገሩ ይታወሳል፡፡

 

ዓለም ላይ ያሉ የአትሌቲክስ አሰልጣኞች የሚወዳደሩበትን ፊልድ በተመለከተ ለጥቃቅን ጉዳዮች ጭምር ትኩረት ሰጥተው በሚያቅዱበት እና በሚፈጽሙበት በዚህ ጠንካራ የውድድር ዘመን ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ግን ቀላል የሆነውን የተፎካካሪዎቻቸውን ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮችን እንኳን ለማቀድ ፍላጎት የሌላቸው መሆናቸው የሆነ የተሳሳተ ነገር ስለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡ 

 

ዕቅድ የሌለው እና ለማቀድ ፈቃዳኛ ያልሆነ ባለሙያ አንድም የዕቅድን ትርጉም አልተረዳም ሁለትም ከእውቀት ማነስ ሊሆን እንደሚችል ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የሚገርመው አንድ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ይሄንን ባለማድረጉ የሚጠየቅበት ስርአት ወይም ፌደሬሽኑ እንዲህ አይነት ባለሙያዎችን ለመጠየቅ አቅም ያጣበት ምክንያት ምንድን ነው የሚለው የቀጣይ የቤት ስራም ይሆናል፡፡

 

አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚዘጋጁበት ሰዓት የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችም በተመሳሳይ መፍትሄ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ከተደረገላቸው በኋላ ተመሳሳይ ፊልድ ላይ ያሉ አትሌቶች እንኳን የማይተዋወቁ እስኪመስል ድርስ በጋራ የመስራት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ለውጤት መጥፋቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን ፌደሬሽኑ አስቀምጧል፡፡

 

ለዚህ ደግሞ በአሰልጣኞች መካከል ያለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት  ሀገራዊ ውድድሮች ላይ እንኳን አትሌቶች በጋራ እንዳይሰሩ እንቅፋት የፈጠረ ሆኗል፡፡ እንደ ዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ አይነት ትልልቅ ውድድሮች ባሉበት ጊዜ ከአየር ጸባይ ጀምሮ እስከ አትሌቶች አመጋጋብ፣ ስነልቦና፣ የተፎካካሪ ሁኔታ በርካታ ትኩረት ለሚፈልጉ ነገሮች እንደ ባለሙያ በጋራ መልስ ለመስጠት ከመስራት ይልቅ በተናጠል የሚደረጉ ዝግጅቶች ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለማሳደራቸው ከተመዘገበው ነገር በላይ ማሳያ ሊኖር አይችልም፡፡

 

ከዚሁ ጋር በተገናኝ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል የሆነው አትሌት የማነ ጸጋዬ የአትሌቲክስ ደላሎች እና አልታዘዝ ያሉ አሰልጣኞች አትሌቲክሱን ገድለውታል ብሏል፡፡

 

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከገጠመው ትልቅ ችግር ለመውጣት በዋናነት ስፖርቱን የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ራሱን ማዘመን እና ወቅቱ ከሚፈልገው ነገር ጋር መጓዝ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ይሆናል፡፡

 

ፌደሬሽኑ ከውስጥም ከውጭም ካሉ ተጽዕኖዎች ራሱን በማላቀቀ  ከምልመላ እስከ ስልጠና እና ውድድር ላሉ ጉዳዮች ወጥ የሆነ አሰራር መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ ደግሞ የተጠያቂነት ስርአትን መዘርጋት፣ እና የባለሙያዎችን አቅም መመዘን ለነገ የሚባል ጉዳይ አይሆንም፡፡ 

 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና የጠፋውን ውጤት ለመመለስ አፋጣኝ ሪፎርም  አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፡፡

 

የዚሁ የሪፎርሙ አካል በሆነ መልኩ ፌደሬሽኑ ትላንት አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር) አዲሱ የጽ/ቤት ኃላፊ አድርጎ መመደቡን አሳውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ለረጅም ጊዜ በርካታ ጥናት እና ምርምሮችን በማድረግ የሚታዩ ለውጦችን ያመጡት ባለሙያው በርካታ ችግሮች ያሉበትን ተቋም ወደ ፊት ለማራመድ ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡

 

ከዚሁ መነሻነት የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ የሚፈልጉ መሰረታዊ የሆኑ የሪፎርም ስራዎች በተቋሙ ይተገበራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

 

ብቻ የፈረሰው የብሔራዊ ቡድን ጉዳይ፣ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና አትሌቶች፣ የአትሌቶች ምርጫ፣ በአሰልጣኞች እና ማናጀሮች መካከል ያለው ግንኙነት፣ የጥቅም ግጭቶች፣ የዝግጅት ሁኔታ  እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች መልስ የሚሹም ይሆናል፡፡

 

በአንተነህ ሲሳይ

 

#ebcdotstream #ebcsport #Ethiopiathletics #reform

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: