Search

አትስሩ ለሚሉን ጆሮ አንሰጥም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሓሙስ መስከረም 22, 2018 37

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጂግጅጋ ከተማ የተከናወነውን የኮሪደር ልማት ሥራ ተመልክተዋል።
ይህ የልማት እና የውበት ሥራ ለአፍሪካ እና ለኢትዮጵያ አይመጥንም የሚሉ አንዳንድ አካሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በነበረው ያልተስተካከለ ሁኔታ ይቀጥሉ የሚል እሳቤ እንዳላቸው አንስተዋል።
በሚሰሩት የልማት ሥራዎች ደስተኞች የማይሆኑት እነሱ ላይም እንደ ኢትዮጵያ ሥሩ የሚል ጥያቄ እየተነሳባቸው በመሆኑ ነው ብለዋል።
ለእንደዚህ አይነት እሳቤዎች ጆሮ መስጠት አያስፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ለእኛ የሚበጀንን እና የሚያስፈልገንን እኛ ነን የምናውቀው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“የሚበጀንን እና የሚያስፈልገንን ከእኛ በላይ ለዜጎቻችን የሚያስብ፤ ከእኛ በላይ ለሀገራችን የሚቆጭ፤ ከእኛ በላይ ልማታችንን የሚያስብ ኃይል አለ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው” ብለዋል።
እንዲህ የሚሉት ኃይሎች የሚጠቅሙን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት ነበረብን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በሠራነው ሥራ እርካታ ሊሰማን ሳይሆን የሚገባው፤ ባለፉት ዓመታት ለምን ይህን ሳንደርግ ቀረን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናልም ብለዋል።
ለማሳያነትም የ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት ዙሪያ ከ 2 እና 3 ዓመታት በፊት የነበረበትን እጅግ የተጎሳቆለ ሁኔታ አስታውሰው፤ በዙሪያችን ያለውን ሰፈር እና የጎረቤቶቻችንን ኑሮ አሻሽለናል ብለዋል።
ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ከተሞች እየተተገበረ የሚገኝ ነው ብለዋል።
ሀገር እንቀይራለን እያልን ከዙሪያችን ካልጀመርን የምናወራው ተረት ተረት ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ችግሮች የሉባትም የሚል መመጻደቅ ተገቢ አይደለም ገና በርካታ ሥራ ይጠበቅብናል ሲሉም አንስተዋል።
በሰለሞን ከበደ