በኢትዮጵያ በተሰሩ እና እየተሰሩ ባሉ ከተማን የማዘመን ሥራዎቻችን በአፍሪካ ምልክትና ምሳሌ እየሆንን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በከተሞቻችን ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ሥራ ተጀምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ከተሞቻችን መድረስ የሚገባቸው ቦታ ላይ ገና አልደረሱም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከኮሪደር ልማቱ ብዙ ሀገራት ተሞክሮ ለመውሰድ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸው፤ የጀመርነው መንገድ በጣም ውጤታማና ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ሀገሪቱ ራሱን የሚወድና የሚያከብር፣ መለወጥና ማደግ የሚፈልግ ህዝብና መንግስት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተባብረን እና በርትተን እንስራ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ