Search

ለኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡- የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

ሓሙስ መስከረም 22, 2018 43

በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ አርሰዴ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
በዓሉን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲንቢሩ፤ በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበትን የኢሬቻ በዓል፣ ባህልና እሴቱን በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር እና የከተሞችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ከበዓሉ ቀናት አስቀድሞም አባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት በዓሉ ወግ እና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለበዓሉ ማክበሪያ ቦታዎች (መልካዎች) 256 የሚሆኑ ቦታዎች ለምተው ለበዓሉ ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በዓሉን ለመታደም ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች እንዲሁም ከኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳ እና ጅቡቲ እንግዶች እንደሚታደሙ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡም እንግዳ ተቀባይነቱን በማሳየትና ባህሉን በማስተዋወቅ ረገድ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ለበዓሉ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች እና መፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
የዘንድሮው በዓልም "ኢሬቻ ለሃገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ መስከረም 24 በሆረ ፊንፊኔ እንዲሁም መስከረም 25 በሆረ አርሰዴ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
በዘሃራ መሃመድ