Search

ለታካሚዎች የሚሰጥ ኦክስጅንን ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ማረጋገጥ ይገባል፡- የጤና ሚኒስቴር

ሓሙስ መስከረም 22, 2018 40

የሕክምና ተቋማት እና ባለሙያዎች ለታካሚዎች የሚሰጥ ኦክስጅንን ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስቴር አስገነዘበ።
ዓለምአቀፍ የኦክስጅን ቀን "የኦክስጅን ተደራሽነትን በማሻሻል፣ ሊድን የሚችልን ሞት መቀነስ" በሚል መሪ ሀሳብ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ተከብሯል።
በመርሐ- ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዎች ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እና ፍሬህይወት አበበ፣ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ፣ የጤና ባለሙያዎች እና አጋሮች ተገኝተዋል።
ከኮቪድ ወረርሺኝ በኋላ በመንግስትና በግል ተሳትፎ በተሰሩ ስራዎች፣ በሀገሪቱ የነበሩ ከ5 የማይበልጡ የኦክስጅን ማምረቻዎችን ወደ 84 ማድረስ መቻሉን ሚኒስትር ዴኤታዋ ፍሬሕይወት አበበ በዚህ ወቅት ገልፀዋል።
በተጨማሪም ባለፉት 5 ዓመታት ከ15 ሺህ በላይ የኦክስጅን ሲሊንደሮችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦክስጅንን ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አስገንዝበው፤ የዓለም ጤና ድርጅትም ከጠቀሜታው አንፃር ኦክስጅንን የሕይወት አድን የሕክምና ግብዓት ውስጥ ማካተቱን አስታውሰዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ በቼክ ሪፐብሊክ መንግስት ድጋፍ የኦክስጅን ማምረቻ በግቢው ውስጥ በመትከል እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በወር 1 ቢሊዮን ብር ለኦክስጅን ግዢ ይወጣ የነበረውን 60 በመቶ ማዳን መቻሉን ነው ያስረዱት።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት በመጓጓዣ መዘግየት እና በተለያዩ ችግሮች ይፈጠር የነበረውን ክፍተት በመቅረፍ፣ ሆስፒታሉ ለታካሚዎች የሚቀርበው የኦክስጅን ጥራትና ተደራሽነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቡን ዶ/ር አብረሀም ገልፀዋል።
በሞላ ዓለማየሁ