ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባውን የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መሠረት በዛሬው ዕለት አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት÷ የግመሉ ጉዞ በውሾች ጩኸት እንደማይቆም ሁሉ የኢትዮጵያ ብልፅግናም የማይቆም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማደናቀፍ ጊዜያችሁን እና ጉልበታችሁን ከምታባክኑ፤ ተባብራችሁ ከግመሉ ጋር ሩጫችሁን እንድታፋጥኑ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያዊያን ካለንበት መነታረክ እና መባላት ወጥተን፤ እንዲህ ባሉ ትላልቅ ሥራዎች የኢትዮጵያን ስም ማስጠራት ብሎም ለልጆቻችን የተሻለ ሀገር መገንባት ሥራችን መሆን አለበት ነው ያሉት።
ድፍን ዓለም ለኢንቨስትመንት የምትመች፣ አመርቂ ዕድገት ያላት፣ ተስፋ ያላት ሀገር እያሉ በከፍተኛ ጉጉት ከእኛ ጋር ሊሰሩ በሚሹበት በዚህ ጊዜ፤ ኢትዮጵያውያን ዓይናችንን ገልጠን በማየት እና በትብብር ሰላምን በማጽናት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
በቢታንያ ሲሳይ