6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መሰረት የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ እንደሚከፍት ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም የ6ኛው ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የተጠናቀቀ ሲሆን፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትም ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በመጪው ሰኞ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን እንደጀመሩ በማብሰር የፌደራል መንግስቱን ዓመታዊ ዕቅድ የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡
የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
ስብሰባው በኢቢሲ ፓርላማ ቻናል፣ በኢቢሲ ዶት ስትሪም እና ሁሉም አማራጮች ይተላለፋል፡፡