Search

በኢሬቻ በዓል የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦች

ዓርብ መስከረም 23, 2018 132

የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ባሕላዊ አልባሳት፣ ምግቦች እና ክንውኖች ይደምቃል፡፡
በኢሬቻ በዓል የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች በማህበረሰቡ ዘንድ ይዘወተራሉ፡፡
አንጮቴ በኢሬቻ በዓል ወቅት የሚዘወተር አንዱ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡
አንጮቴ የሥራ-ሥር ዘር ሲሆን በተወሰኑ አካባቢዎች የሚበቅል እና በወለጋ አካባቢ በስፋት የሚዘወተር ምግብ ነው፡፡
አንጮቴ ከተቀቀለ በኋላ በቂቤ ተለውሶ ለምግብነት ይቀርባል፡፡ በሌላ መልኩ፣ የተቀቀለው አንጮቴ ከቆጭቆጫ ጋር ቀርቦ ሊበላም ይችላል፡፡
ይህ ባሕላዊ ምግብ ሰውነትን ለመገንባት እና ለመድኃኒትነት እንደሚውል ይገለጻል፡፡
ግሪሴ የተባለው ባሕላዊ ምግብ ደግሞ፣ በድሮ ጊዜ አባቶች ለአደን ሲወጡ እናቶች በአገልግል እንደ ስንቅ የሚያስሩላቸው የምግብ ዓይነት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከቀይ ጤፍ እንደ ቂጣ ተዘጋጅቶ በቂቤ ታሽቶ የሚዘጋጀው ጨጨብሳ፣ አሁን አሁን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚዘወተር እና ተወዳጅ የምግብ ዓይነት ነው፡፡
ከገብስ ዱቄት በቂቤ ታሽቶ የሚዘጋጀው ጭኮ፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ እና በተለዩ ባህላዊ ክንውኖች ወቅት የሚዘጋጅ እንዲሁም በስጦታ መልክ የሚቀርብ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡
ቡነ ቀላ የተባለው ባሕላዊ ምግብ የገብስ ቆሎ፣ ድፍን ቡና እና ዝንጅብል በቂቤ ታሽቶ የሚዘጋጅ ሲሆን በዓመት በዓል እንዲሁም የተከበረ እንግዳ ሲመጣ የሚቀርብ ነው ፡፡
በኢሬቻ በዓል ወቅት ከሚዘወተሩ ባሕላዊ ምግቦች ውስጥ በቂቤ ታሽቶ የሚቀርበው ቆሪ የተባለው የገብስ ቆሎ ነው፡፡
መሮ የተሰኘው ባሕላዊ ምግብ እሸት(ለጋ) በቆሎ ተፈጭቶ በእንፋሎት ብቻ የሚበስል ሲሆን በተመሳሳይ መሮ በቀይ ጤፍም ይዘጋጃል፡፡
ለተከበረ እንግዳ እንዲሁም ለበዓል የሚዘጋጀው ጩንቦ፣ ጥቁር ጤፍ ከተጋገረ በኋላ በሚጥሚጣ እና ቂቤ ተቀብቶ አይብ እና ቆጭቆጫ ተደርጎበት ለምግብነት ይቀርባል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ