Search

እንደ ኢሬቻ ያሉ በዓላትን የአንድነት እና ኅብረት ማጠናከሪያ ልናደርጋቸው ይገባል - የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር

ዓርብ መስከረም 23, 2018 29

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ለዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በመልዕክታቸው፣ “ዓለም ስለ ዴሞክራሲ ሥርዓት እምብዛም ትኩረት ባልሰጠበት ዘመን፣ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱ ሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ባህል ያዳበረ ትልቅ ሕዝብ ነው” ብለዋል።

ይህ ሕዝብ ካለው አኩሪ እና ቀደምት ባህሎች ውስጥ አንዱ ደግሞ የገዳ ሥርዓት ትሩፋት የሆነው የኢሬቻ በዓል መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ኢሬቻ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የወንድማማችነት እና የምስጋና በዓል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ በኢሬቻ ያሉ ባህላዊ እሴቶች፤ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና እና ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላቸው ሚና እጅግ የላቀ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የሕዝብ በዓላት የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን በማጠናከር፣ የሕዝቦች አብሮነትን በማጎልበት፣ የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚሰጠው ፋይዳ እጅግ የጎላ በመሆኑ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል የተጀመረው ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እንደ ኢሬቻ ያሉ ታላላቅ ክብረ በዓላትን የሀገራችን አንድነት እና ኅብረት ማጠናከሪያ ስፍራ፤ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶቻችን ማሳኪያ መንገድ፤ ለበለጠ ስኬት እና ለላቀ ውጤት የምንሰበሰብበት መድረክ በማድረግ፣ ለበለጠ ድል እንነሣ ሲሉ ጠይቀው፣ መልካም የኢሬቻ በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል።

#EBC #Irreecha #Ethiopia #ኢሬቻ