በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ጉጂ ዞን በሰላም እና ፀጥታ ሥራ ላይ ለተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት የምስጋና እውቅና ሰጥቷል።
የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ብዙነህ፤ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ምክንያት ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር በሚፈለገው ደረጃ ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና ዛሬ ላይ ሰላም በመስፈኑ ችግሩን እንደታሪክ ለማውራት እንድንበቃ ላደረጉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል።

ለሰላም ማስፈኑ ሥራ ውድ ሕይወታቸውን ሰጥተው ቀና ብለን እንድንሄድ ላደረጉን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ምስጋና መስጠት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
እንደተቋም ለተከናወኑ የሰላምና ደኅንነት ጥበቃ ሥራዎች የጉጂ ሕዝብ እና አስተዳደር ለሰጠን ዕውቅና አክብሮታችን የላቀ ነው ያሉት የመከላከያ ሠራዊት የኮሩ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ግርማ አየለ ጉርሙ፤ የተሰጠን እውቅና የሠራዊቱን እና የሕዝባችንን ትሥሥር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ሠራዊቱ ከአካባቢው የፀጥታ አካላት እና ከማኅበረሰቡ ጋር በሠራቸው የፀጥታ ሥራዎች ተቀዛቅዞ የነበረው የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃቱ ተገልጿል።