የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሲዊዲን፣ በኖርዲክ ሀገራት እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተወካዮችን ለማስመረጥ ያዘጋጀው መድረክ በስቶክሆልም ከተማ ተጀምሯል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ሥላሴ፥ ተሳታፊዎች የምክክር መድረኩ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚኖረውን ሚና በመረዳት ለመሳተፍ በመምጣታቸው በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ ሁሉም ህብረተሰብ እየተሳተፈበት ያለ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ይህንን በታሪክ ተደጋግሞ የማይገኝ አጋጣሚ እውን ለማድረግ በጋራ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም ይህ ታሪካዊ እድል ለውጤት እንዲበቃ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን የአካታችነትና አሳታፊነት መርህን ተግባራዊ በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ምክክር እያካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።
በነዚህ ውይይቶች ሀገራችንን በፅኑ የዴሞክራሲ መሰረት ላይ ለመገንባትና የተረጋጋች ሀገር ለመፍጠር የሚያስችሉ አመላካች መፍትሄዎችን እየተመለከትን ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ በውጪ የሚኖሩ ኢትጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል በሚል እምነት በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ በሲዊዲን ስቶክሆልም እየተካሄደ ያለው መድረክም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
የዲያስፖራ ማኅብረሰቡ በአገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ አሁን ደግሞ ለአገራችን ዘላቂ ሰላም ቁልፍ በሆነው በአገራዊ ምክክር ላይ አጀንዳዎቻቸውን በነጻነት በመስጠት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራት እንዲሁም በዚህ መድረክ ስለሚያከናውኑት ተግባር በኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ገለጻ ተደርጎላቸው ተሳታፊዎቹም በየቡድኑ ተከፋፍለው በመወያየት አጀንዳዎቻቸውን በማጠናቀር ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።