የኢቲቪ ፓርላማ ቻናል ስርጭት የሕዝብ ተሳትፎን እና የዴሞክራሲ ባህልን ያሳድጋል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢቲቪ ስርጭት ለመጀመር ላለፉት ዓመታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አፈ ጉባኤው አስታውሰዋል።
ስርጭቱም በሀገሪቷ ላይ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እና የተለያዩ እቅዶችን በምንገመግምበት ጊዜ የሕዝቡን ጥያቄ እና ቅሬታ በቀጥታ እንድናስተላልፍ እና መፍትሄው ላይ በትኩረት እንድንሰራ ያስችለናል ብለዋል።
አክለውም የቀጥታ ስርጭቱ የፓርላማውን የሥራ አፈፃፀም ሂደት ለሕዝቡ በማድረስ የማያግባቡ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልፀዋል።
ራሱን በይዘትና አቀራረብ እያዘመነ የመጣው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ ነገ መስከረም 26 ቀን 2018 የኢቲቪ ፓርላማ ቴሌቪዠን ቻናሉን በይፋ ሥራውን ያስጀምራል።
በሄለን ተስፋዬ