Search

በወላይታ በመሬት መንሸራተት የተፈናቀሉ 100 ቤተሰቦች የተገነቡላቸውን ቤቶች ተረከቡ

ሰኞ መስከረም 26, 2018 45

በወላይታ ዞን በ2016 ዓ.ም በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ 100 ቤተሰቦች በአባያ ጫዎ ካሬ መጠለያ መንደር የተገነቡላቸውን ቤቶች ተረክበዋል።

ቤቶቹን የርክክብ መርሐ-ግብር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የወላይታ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

ለነዋሪዎች ማኅበራዊ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራም መከናወኑን የዞኑ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት አስታውቋል።

ለ6 ወር የሚሆን ቀለብ፣ የውሃ ቦኖ እንዲሁም የጤና እና የፀጥታ ተቋማት መገንባታቸውን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ ተናግረዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ፥ ነዋሪዎች የግብርና ምርቶችን አምርተው እንዲጠቀሙ ለእያንዳንዳቸው በተዘጋጀላቸው 1 ሄክታር ማሳ ላይ ዘር መዝራት እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ 25 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ እና ምግብ ነክ ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፥ ነዋሪዎቹን ለማስፈር የክልሉ መንግሥት የራሱን ድርሻ በላቀ ደረጃ መወጣቱን ተናግረዋል።

ቀሪ 200 አባወራዎችን የማስፈር ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል ብለዋል።

በአዲሱ መንደር የሰፈሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው፥ ቀድሞ የነበሩበት ስፍራ የስጋት ቀጣና መሆኑን አንስተው፣ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በመርሐ-ግብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላን ጨምሮ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በተመስገን ተስፋዬ

#ebcdotstream #ethiopia #southethiopia #wolaita