በትውልድ ላይ የሚታየው ስብራት ዋነኛ መንስኤ በሆነው የትምህርት ጥራት ላይ በተለየ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
መንግሥት ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ መደበኛ እና መደበኛ ት/ቤቶች ግንባታን እያስፋፋ መሆኑን እና በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ፕሬዚዳንቱ የጠቆሙት።
መንግሥት ለመጪው ትውልድ ሰፊ ትኩረት ይሰጣል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሕጻናት ዕድገት እና ትምህርት ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የሴቶች የትምህርት ተሳትፎን ማሻሻልም መንግሥት በልዩ ትኩረት የሚሠራው እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል።
የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ኢኮኖሚው የሚፈልጋቸውን፣ እጃቸው የሰላ እና ምርታማነትን የሚያረጋግጡ ባለሙያዎችን በሚያፈራ መልኩ እንደሚቃኝም ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካዳሚያዊ ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ፤ በአስተዳደር እና በሰው ኃይል ልማታቸውም የተሻሉ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ፕሬዚዳንት ታየ ገልጸዋል።
መንግሥት በአርብቶ አደር አከባቢ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በልዩ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ጥቅል ተሳትፎን እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉ ሌላው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተከናወነ ሥራ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና መገኘቱን ገልጸዋል።
"ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ ማኅበረሰቡን በማንቀሳቀስ የትምርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወነው ሥራም ለትምህርት ጥራት መሻሻል የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ነው ፕሬዚዳንቱ ያነሱት።
#EBC #ebcdotstream #parlament #education #educationquality #schools