Search

የተማሪዎችን ክህሎት በማበልፀግ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ያለመው ዲጂታል ቤተመጻሕፍት

ሰኞ ታኅሣሥ 20, 2018 96

የዲጂታል ቤተመጻሕፍቱ ሥራ መጀመር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የጀመርነውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ሲሉ በታርጫ ከተማ የሂዶታ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ።

በለማ እና ዶክተር ጉነት ፋውንዴሽን ድጋፍ የተደራጀው የሂዶታ ዲጂታል ቤተመጻሕፍት ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የዲጂታል ቤተመጻሕፍቱ ሥራ መጀመር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የጀመርነውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢቢሲ የሰጡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ከቴክኖሎጂ ጋር ያለንን ቅርርብ የተሻለ በማድረግ ጊዜያችንን በአግባቡ የምንጠቀምበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።

ቤተመጻሕፍቱን መርቀው የከፈቱት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች በካሎ (ዶ/ር)፥ ቤተመጻሕፍቱ የተማሪዎችን ዲጂታል ክህሎት በማጎልበት ተወዳዳሪነታቸውን ያሳድጋል ብለዋል።

እንደ ሀገር ለተጀመረው የዲጂታል ጉዞ ስኬት በአካባቢው ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት ዶ/ር አማረች፤ ዜጎች ከቴክኖሎጂ ጋር ተላምደው ውጤታማ እንዲሆኑ ተገቢው ክትትል ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ  አቶ አልማው ዘውዴ፥ ዲጂታል ቤተመጻሕፍቱ የፈተና አስተዳር ሥርዓትን ለማዘመን የተጀመረውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።

የተማሪዎችን በራስ የመተማመን አቅም በመፍጠር ሂደትም ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸው፤ ተሞክሮውን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው፥ የዲጂታል ቤተመጻሕፍቱ ሥራ መጀመር የዞኑ አስተዳደር ለጀመረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨማሪ አቅምን ይፈጥራል ብለዋል።

በየዓመቱ ላቅ ያለ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው የሂዶታ አዳሪ ትምህርት ቤት ውጤቱን አስጠብቆ እንዲዘልቅ ከማስቻል በተጨማሪ የነበረበትን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።

በዳውሮ ልማት ማህበር ስር የሚገኘው ሂዶታ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ብሔራዊ ፈተና ያስፈተናቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስገባት የቻለ ውጤታማ ትምህርት ቤት መሆኑም ተገልጿል።

በሰለሞን ባረና

#EBC #ebcdotstream #HidotaBoardingSchool #DigitalLibrary