Search

ሀሰተኛ የሙያ ብቃት ምዘና ሰርተፍኬትን ለመከላከል ጠንካራ ሥራ መስራት ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሓሙስ ታኅሣሥ 02, 2018 85

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሀሰተኛ የሙያ ብቃት ምዘና ሰርተፍኬትን ለመከላከል ጠንካራ ሥራ መስራት እንደሚገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመስክ ምልከታ ማድረግ ጀምሯል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (/) ሚኒስቴሩ ከኤጀንሲዎች ጋር የሚሰራበት፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሥራ ፈላጊዎችን የሚመዘግብበትና የሚለይበት ስርዓት ተደራሽነቱን በመስፋት ምን ያህል ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳሉ አንስተዋል፡፡

ቴክኖሎጂውና አሰራሩ ላይ ግንዛቤ ከማስጨበጥ፣ ተገልጋዮች እውቀቱ ኖሯቸው እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንፃር የተሰሩ ሥራዎችን በተመለከተ እና የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ላይ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ከመላክ አኳያ ያለበት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ሰልጣኞች ከሀገር ውስጥ ባሻገር በዓለም የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የስልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ ዘመናዊ የማሰልጠኛ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አኳያ ያሉበትን ሁኔታ ሰብሳቢው አንስተዋል፡፡

ከሙያ ብቃት ምዘና ሰርተፍኬት ጋር በተያያዘ የምዘና ማዕከላት ሀሰተኛ ማስረጃ መስጠት ብቻ ሳይሆን ስልጠናቸውን በአግባቡ ሳያጠናቅቁ ለማሳለፍ የሚሞክሩና በገንዘብ የሚደልሉ አካላትን በመቆጣጠር ከዚህ ችግር እንዲወጡ የማድረግ ስራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አኳያ ወጣቱ በፋይናንስ አቅርቦት፣ በገበያ ትስስር፣ ከኢንተርፕራይዞች ሽግግር አንጻር ምን ያህል ሀብት እያፈሩ እንደሆነ ግልጽ በሆነ መንገድ መቀመጥ እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው በክትትልና ድጋፍ ሥራው ያልተቋረጠ ግብረ መልስ በመስጠት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ትልቅ ሚና እንደነበረው አንስተው፤ የሥራ እንቅስቃሴያችንን በአካል ለማየት እዚህ መገኘታችሁ የበለጠ አቅም ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዕቅድ ዝግጅት ሥራውን ከተጠሪ ተቋማት እና ከክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዳዘጋጀ ገልፀው፤ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት የተቋም ግንባታ ሥራዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱም አስረድተዋል፡፡

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሥራን በሚመለከትም የዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ምዕራፍ እንደተሸጋገረሩም አብራርተዋል፡፡

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #ParlamaNews