የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እያንዳንዱ ዜጋ ሊያስተጋባው እና ለውጤታማነቱም በጋራ ሊሠራበት የሚገባ ታሪካዊና ወቅታዊ ጉዳይ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
አዲሱ ትውልድ የብሔራዊ ጥቅምን አስፈላጊነት ተገንዝቦ እንዲያድግ የባሕር በር እና ቀጣናዊ ጉዳዮች በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት እያገለገለ የሚገኘው የ6ኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስ መማሪያ መጽሐፍም ትውልዱ ስለቀጣናዊ ጉዳዮች ያለውን ግንዛቤ እንዲያሳድግ የሚረዱ የተለያዩ መረጃዎችን ይዟል።
መጽሐፉ የባሕር በርን አስፈላጊነት፣ የምስራቅ አፍሪካ አጎራባች ሀገራትን መልክዓ ምድር እና አዋሳኝ የውኃ አካላትን በዝርዝር ይዳስሳል።
በመጽሐፉ ተማሪዎች ስለ ሀገራቸውና ስለ አህጉራቸው ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድጉ መረጃዎች በሰፊው ተካተዋል። መጽሐፉ የባሕር በር ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በማብራራቱ፣ ታዳጊዎች ስለ ቀይ ባሕር ምንነትና ፋይዳ በጥልቀት እንዲገነዘቡ ዕድል ፈጥሯል።
ኢቲቪ ያነጋገራቸው የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች እንደገለጹት፤ የባሕር በር ለወጪና ገቢ ንግድ ወሳኝ መሆኑን በትምህርታቸው ተረድተዋል።
ጠንካራና ግዙፍ የሆነችው ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ቢኖራት፣ የንግድ እንቅስቃሴዋን ከዓለም ሀገራት ጋር በሰፊው ለማሳለጥና ለኢኮኖሚ እድገቷ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምታስተዳድረው የእራሷ የባሕር በር ስለሌላት በኢኮኖሚዋ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተማሪዎቹ ይገልጻሉ።
በተለይም ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ከፍተኛ ገንዘብ ለሀገር ኪሳራ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ያጣችውን የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘባቸውን ያስረዳሉ።
በሜሮን ንብረት