"Pulse of Africa" በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀደምትና ታዋቂ ከሆኑ ሚዲያዎች አንዱ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "Pulse of Africa"የተሰኘ የፓን አፍሪካ ሚዲያን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ "Pulse of Africa" በጣም ቀለል ያለ ጅማሮ ያደረገ ቢመስልም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀደምት እና ታዋቂ ከሆኑ ሚዲያዎች አንዱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።
የአንድ ሀገር ሚዲያ እድገት ከሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ጋር የተሳሰረ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።
በትርክት ሰውን፣ ማህበረሰብን፣ ሀገርንና አህጉርን መስራት እንደሚቻለው ሁሉ ትርክት ግለሰብን፣ ማህበረሰብንና ሀገርን የማፍረስ አቅም እንዳለው አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምስቅልቅል ውጤት የገነባነው በትርክት ነው ሲሉም የትርክትን ወሳኝ ሚና አብራርተዋል፡፡
እንዳንተማመን፣ እንዳንግባባ፣ እንዳንከባበር፣ እንዳንተጋገዝ፣ በጋራ እንዳንቆም ያደረገን ትርክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገራዊ ትርክት ላይ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አፍሪካ ጥልቅ ሳለች ትንሽ መስላ እንድትታይ የተሰራበት ዋናው ምክንያት በትርክት ጭንቅላትን ለመመገብ የአፍሪካ ሀገራት የነበራቸው ዝግጁነት ውስን ስለሆነ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
የ"Pulse of Africa" ሚዲያ በአፍሪካ ቀዳሚ እና ተፈላጊ የመሆን ህልሙ እንዲሳካ በትጋት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
#EBC #ebcdotstream #AbiyAhmed #pulseofafrica