የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታ የታየው የአመለካከት ለውጥ የተሻለ ለመሥራት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ዘርፈ ብዙው የስነ-ጥበብ ሰው መምህር ሰለሞን ደሬሳ፤ በርካታ ኢትዮጵያዊ ላሊበላ እና አክሱም ፊት ቆሞ ቀድሞ የሚያስበው ቅርሶቹ እንዴት እንደማይሰሩ ነው ማለታቸውን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ ይህም ሀገር ለመቀየር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ትልቁ ፈተና የአመለካከት ችግር መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የተሻለ ጥራት እና ንጽህና ለማግኘት ቦታ መቀየር አለብኝ የሚል እንጂ ያለሁበትን ቦታ ማሻሻል አለብኝ ብሎ ያለማሰብ ችግርም እንዳለ አቶ ጌታቸው አንስተዋል።
በዚህ ረገድ የተሻለ አኗኗር ለማግኘት ወደከተማ መዛወር አለብኝ የሚል እሳቤ አያስፈልግም ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ይህንን አመለካከት ለመስበር የሚያስችል ሥራ በሞዴል የገጠር መንደሮች አማካኝነት ተሰርቷል ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ ሥራ አመራሩ በመኖሩ የተፈጠረ ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለተጨማሪ አቅም ጉልበት የሚፈጥርም ነው ብለዋል።
የሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታ በታቀደ መልኩ ከተማ ለመፍጠር ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።