በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በናይሮቢ፣ ኬንያ “ዲጂታላይዜሽንን ለቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት መጎልበት በመጠቀም ለዘላቂ እና አካታች ዕድገት ማዋል” በሚል ጭብጥ በተካሄደው 24ኛው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) የመሪዎች ጉባዔ ተሳትፏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር፥ አሁን ያለንበት ወቅት ቴክኖሎጂ ሁሉንም ነገር እየቀየረ የሚገኝበት እጅግ ወሳኝ ወቅት ነው ብለዋል።
ቴክኖሎጂ ከወትሮው በተለየ በፍጥነት እያደገ የሀገራትን የዕድገት አቅጣጫ፣ የማኅበረሰብን ግንኙነት እና ሀገራት ብልፅግናን እንዴት እንደሚጋሩ እየወሰነ ይገኛል ነው ያሉት።
"አሁን ጊዜው አፍሪካ ቁጭ ብላ የምትጠብቅበት አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፈጠራ ችሎታ ያለው ሕዝብ እና ለብልፅግና የሚያበቃ የተፈጥሮ ሀብት የታደለችው አህጉር የሚገባት ዕድገት ላይ እንድትደርስ ወቅትቱን የዋጀ ሥራ መሥራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ለአፍሪካ የሚገባትን ብልፅግና ለማሳካት በጋራ ለጋራ ዓላማ መሰለፍ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም ቀጣናዊ ተቋማት ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አመላክተዋል።
"የዚህ ዓመት ትኩረታችን ዲጂታል ሽግግርን ለአካታች ቀጣናዊ ዕድገት ማዋል ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዲጂታል ሸግግር የአፍሪካን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ታሪክ እንደ አዲስ ለመፃፍ የሚጠቅም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህም ሕዝባዊ ዲጂታል መሠረተ ልማትን በማስፋፋት እና ፍትሐዊ ተደራሽነቱን በማረጋገጥ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ማንነቱን እና አቅሙን እንዲያውቅ በማድረግ የሚሳካ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
የዲጂታል ደኅንነትን በማረጋገጥ፣ ተደራሽነቱን በማሻሻል፣ ፍትሐዊነቱን በማረጋገጥ እና ድንበር ተሻጋሪ ግንኙነቶችን በማጠናከር ዓላማውን ማሳካት እንደሚቻልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለው ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #COMESA #Kenya #Ethiopia #AbiyAhmedAli