Search

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በ2025 የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ - ዓለም ባንክ

ማክሰኞ መስከረም 27, 2018 151

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በ2025 የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ የዓለም ባንክ ሪፖርት አመለከተ፡፡

ዓለም ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በፈረንጆቹ 2025 በ3.8 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ጠቁሟል፡፡

ባንኩ የአፍሪካ የግማሽ ዓመት ሪፖርት በሚል ባወጣው መረጃ እንዳመለከተው በቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ኮትዲቯር የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ ብሏል፡፡

3ቱ የአኅጉሪቱ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤቶች ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ከሳሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የዋጋ ንረት እየተረጋጋ እንደሚገኝ የገለፀው ሪፖርቱ፤ ለአብነትም ኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የወሰደችው እርምጃ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱንና የወለድ ምጣኔ እንዲቀነስ እድል መፍጠሩን ጠቁሟል፡፡

በቀጠናው ሀገራት ያለው ምቹ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ከተተነበየው ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት ከ3.5 በመቶ ወደ 3.8 በመቶ እንዲያድግ ማስቻሉንም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ይህም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን እንዲሻሻል በማድረግ የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጥራል ብሏል፡፡

ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 47 ሀገራት መካከል 30ዎቹ ከዚህ ቀደም ከተተነበየው የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡም ነው ባንኩ የገለፀው፡፡

የቀጠናው ኢኮኖሚ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ 2026 ዓመትም በ4.4 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብም የዓለም ባንክ ሪፖርትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በላሉ ኢታላ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Sub_Sahara_Africa #Economic_Growth