ከዚህ በፊት አንድ ሥራ ሲሠራ አንችልም የሚል አስተሳሰብ ቢኖርም በተግባር ሰርቶ በማሳየት ኢትዮጵያ ትችላለች ብሎ የሚያምን እሳቤ እየተፈጠረ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
አንድ ሥራ ሲሠራ እንዴት እንደማይቻል ብቻ የሚያይ እና ከተቻለም ለመካድ የሚደረገው ሙከራ አደገኛ መሆኑን አንስተው፤ ኮሪደር ልማት ሲሠራ ማን ዲዛይን አደረገላቸው? ማን ሠራቸው? ገንዘቡ ከየት መጣ? የሚሉ ጥያቄዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ይህም ይቻላል ብሎ ከማሰብ ይልቅ አይቻልም ብሎ የሚያስብ መኖሩን ያመላክታል ሲሉ አስረድተዋል።
የኩሽ፣ የአክሱም፣ የፑንት ስልጣኔ የነበረበት ሀገር አሁን ከዚያ ያነሰ ሥራ ሲሠራ ማን ሠራላቸው ብሎ ሌላ ባለቤት ፈላጊ መሆን እንደማይገባም አንስተዋል።
አሁንም ሞዴል የገጠር መንደሮችን የሠራቸው የሌላ ሀገር ነው ብለው የሚያስቡ መኖራቸውን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን ላይ እንችላለን ብሎ በማመን ጉዳይ ውስንነት እንዳለ አመላክተዋል።
የእሳቤ ስብራት በተግባር ቁምነገር እንዳንሠራ ያደርገናል፤ ሆኖም እኛ እንችላለን፣ የማንችለው አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል።
እንዳንችል ያደረገን የአቅጣጫ ስህተት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ከተስተካከለ ደግሞ እንደሚቻል በተግባር ታይቷል ብለዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ