ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የታመነበትን ግዙፍ የአፈር የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት አቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች።
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው የግብርና ዘርፉን እድገት የሚወስን ፕሮጀክት መሆኑን የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምህሩ ሞኬ ገልጸዋል።
በ40 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ ተግባር የገባው ይህ ፕሮጀክት በርካታ የሥራ እድሎችን እንደሚፈጥር የጠቀሱት ኃላፊው፤ ይህም የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።
የፋብሪካው መገንባት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ እና ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበረውን የማዳበሪያ አቅርቦት ሰንሰለት በማሳጠር ምርታማነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ይሻጋገራል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው፤ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደገው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ በሀገር ሰርቶ በሀገር መኖር የሚለውን ሃሳብ ወደ ተግባር የቀረና የሁሉምን ልብ ያረጋጋ ነው ብለዋል።
ፋብሪካው ወደ ሥራ ከአቅርቦት ማነስ፣ ከውጪ ምንዛሬ እና ከወቅት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ይቀርፋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር፤ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ውስጥ በስፋት እንድትገባ እንዲሁም የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
በሴራን ታደሰ