Search

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ቆም ብለን ራሳችንን እንድናይ አድርጎናል - ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)

ዓርብ መስከረም 30, 2018 60

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ቆም ብለን ራሳችንን እንድናይ አድርጎናል ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ገለፁ።

በመደመር መንግሥት መፅሐፍ ዙሪያ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ሌሎች ሀገራት ለምን አላደግንም፤ ለምን አልተቀየርንም፤ ምንድነዉ የችግሮቻችን መንስኤ የሚለዉን የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ተንትነን እንድናይ አድርጎናል ብለዋል።

መዋቅር ላይ በደንብ አለመሰራቱ፣ አስተሳሰብ ላይ ያሉ እክሎች፣ ያሉትን ሀብቶች ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ የእድገት ሽግግር ማምጣት አለመቻሉ ለእድገት አንቀፋት እንደሆነም አንስተዋል።

የባከነዉን ይህን እድል በማካካስ የህዝቡን ፍላጎት በማሟላት ለመጪው ትዉልድ ትሩፋት በማስቀመጥ በፍጥነት መጓዝ እንደሚያስፈልግም በመፅሐፉ በግልፅ መቀመጡን ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማካሪ ቋሚ ኮሚቴ አባል አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለግብርና ስራ የተመቸ መሬትና ተስማሚ የአየር ንብረት ቢኖራትም ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማገዝ ባለመቻሉ ተገቢው ጥቅም አለመገኙትን መፅሐፉ በዝርዝር እንደሚዳስስ ገልጸዋል።

መፅሐፉ የኢትዮጵያ ግብርና በቴክኖሎጂ ቢታገዝ እና እሴት ቢጨመርበት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋልታ የሚሆንበት እድል ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያብራራ ተናግረዋል፡፡

ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ለዘመናት የቆየው ባህላዊ የእርሻ ዘዴ በመቀየር በዘመናዊ የመስኖ ስልቶች መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ዘርፉን ለማሳደግ ግብርናን ማዘመን፣ የግብርና እሴት ሰንሰለትንና የገበያ ትስስርን ማስፋፋት እንዲሁም በዘርፉ ያሉትን የፖሊሲ እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በትብብር መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በቢታንያ ሲሳይ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #yemedemermengist