Search

መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ቅዳሜ ጥቅምት 01, 2018 74

መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የችሎት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ዳኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል።

አቶ ታገሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የዳኝነት ሥራን ሀገርን እና ሕዝብን በማስቀደም በትጋት፣ በብቃት እና በታማኝነት ማከናወን ያስፈልጋል።

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተጀመረው አሠራርን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሂደት ፍትህን በጥራት እና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ በመሆኑ በሌሎችም አካባቢዎች መስፋፋት ይኖርበታል ብለዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፥ "ውጤታችን መለካት ያለበት በስኬታችን ብቻ ሳይሆን በትከክለኛ አቅጣጫ ተጉዘን በደረስንበት ደረጃ ጭምር መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በፍርድ ቤቶች አሠራር እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በ2017 ዓ.ም የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን እንዲሁም በ2018 ዓ.ም ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ሥራዎችን ዘርዝረዋል። 

በዚህ ዓመት በዕቅድ የተያዙ ሥራዎችን የማጠናቀቅ እና የመጪውን ዘመን ፍኖተ ካርታ የመቀየስ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 በከፊል ዝግ የነበረው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የችሎት አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

በምንተስኖት ይልማ

#ebcdotstream #courts #justice #justicereform